
ባሕር ዳር: ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የደቡብ ጎንደር ዞን በደራ፣ ፎገራ እና ሊቦከምከም ወረዳዎች ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ስጋት ታሳቢ ያደረገ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን መሥራቱን አስታውቋል፡፡
የክረምት ወራት መግባትን ተከትሎ የጎርፍ አደጋ፣ የመሬት መንሸራተት እና ሌሎች አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡ በደቡብ ጎንደር ዞን ከክረምት መግባት ጋር ተያይዞ በደራ፣ በፎገራ እና በሊቦ ከምከም ወረዳዎች የጎርፍ አደጋ ስጋት ይከሰታል፡፡ ትርፍ አምራች በኾኑት ወረዳዎች የሚከሰተው የጎርፍ አደጋ በሰዎች፣ በሰብል ልማት እና በእንስሳት ላይ ጉዳት ሲያደርስ ኖሯል፡፡ ዘንድሮም የጎርፍ አደጋ ሊፈጠር ይችላል የሚል የአካባቢውን ነዋሪዎች ስጋት ገብቷቸዋል፡፡ የርብ እና የጉማራ ወንዞች ደግሞ የጎርፍ አደጋ ምክንያቶች ናቸው፡፡
በፎገራ ወረዳ ሽና ቀበሌ ነዋሪው ዝጋለ ውቤ ከጎርፍ ተጋላጭ እንዳይኾኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሢሠሩ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡ ባለሙያዎች ድንገተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ ሊኖር ይችላል በሚል የማስጠንቀቂያ ምክር እየሰጧቸው መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ በመሬት ላይ ያለ እህል ከፍ ወደ አለ ቦታ እንዲቀመጥ፣ ሕጻናት፣ አረጋውያን እና እንስሳት እንዳይጎዱ ጥንቃቄ እንዲደረግ እያሳሰቡ ነው ብለዋል፡፡
የጎርፍ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች እየደለደሉ እና እየከተሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ከሚሠራው ሥራ በላይ የኾነ የጎርፍ መጥለቅለቅ ሊኖር ይችላል የሚል ስጋት አለን ነው ያሉት፡፡ በክረምት ወቅት ሁልጊዜም የጎርፍ አደጋ ስጋት እንዳለባቸውም አንስተዋል፡፡ “የለመድነው ሙላት ነው አታሟርቱብን” በሚል የቅድመ ዝግጅቱን ሥራ ችላ የሚሉ መኖራቸውንም ነግረውናል፡፡ ባለሙያዎች የሚሉትን ሰምቶ መጠንቀቅ እንደማይጎዳም ገልጸዋል፡፡
የአቧ ኮኪት ቀበሌ ነዋሪው ጌታቸው ምትኩ ከባለሙያዎች ጋር በመኾን የአፈር መከተር ሥራ ሢሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ከክረምቱ መክበድ ጋር ተያይዞ በአፈር የተደለደለው አካባቢ እየተንሸራተተ ነው ብለዋል፡፡ በአካባቢው ከፍተኛ የጎርፍ ስጋት መኖሩንም ገልጸዋል፡፡
ክረምት በገባ ቁጥር በዘላቂነት ከጎርፍ ስጋት የሚወጡበት የጎርፍ መከላከል ሥራ እንዲሠራላቸውም ጠይቀዋል፡፡
የደቡብ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በላይ አስራደ በደራ፣ ፎገራ እና ሊቦ ከምከም ወረዳዎች ላይ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውን አስታውቀዋል፡፡ በጎርፍ የሚጠቁ 23 ቀበሌዎች መኖራቸውንም ኀላፊው ገልጸዋል፡፡ በጎርፍ ተጋላጭ በኾኑ ቀበሌዎች ማኅበረሰቡ ላይ ሊደርስ የሚችለውን የሰብል ምርት፣ የእንስሳት እና የማኅበራዊ ተቋማት ኪሳራ ታሳቢ በማድረግ ከክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ጋር በመኾን በበጋ ወራት የቅድመ መከላከል ሥራ ሢሠራ መቆየቱንም አንስተዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት በፈቀደው በጀት መሠረት 25 ኪሎ ሜትር የጎርፍ ማፋሰሻ እና መከላከያ መከተሪያዎች መሥራታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብም በኬሻ አፈር በመሙላት የማሳውን ዳር እና ዳር፣ የመኖሪያ ቤቱን አካባቢ እየገደበ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ ከዚህ ሁሉ ዝግጅት በኋላ የጎርፍ መጥለቅለቅ ቢፈጠር ከችግሩ ለመውጣት ጀልባዎች መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል፡፡ የውኃ ዋና የሚችሉ ወጣቶችን መልምለው ማዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡ የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ ሲፈጠርም ማኅበረሰቡን የሚነግሩ በጎ ፈቃደኞች መኖራቸውንም አመላክተዋል፡፡
የጎርፍ አደጋ ቢከሰት ምላሽ የሚሰጥ ዐቢይ እና ቴክኒካል ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ነዋሪዎችን በጊዜያዊነት ማስጠለል ቢያስፈልግም ጊዜያዊ መጠለያ፣ የጤና አገልግሎት እና ሌሎች በቅድመ ዝግጅት ሥራው የተሠሩ ሥራዎች ናቸው ተብሏል፡፡
የጎርፍ መጠለቅለቅ እና በማኅበረሰቡ ላይ የሚያሳድረው ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው ሙሉ በሙሉ ከስጋት ነጻ ለማድረግ በጥናት የተደገፈ ሥራ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ እኛ ማስታገሻ እየሠራን ነው፣ ጥናት እየተጠና ነው፣ ጥናቱ መልስ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ሊከሰት ከሚችለው የጎርፍ አደጋ ራሳቸውን ለመጠበቅ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በተለይም በጎማራ እና በርብ አካባቢ ጥንቃቄ ይሻል ነው ያሉት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!