
ደብረ ታቦር: ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የክረምት በጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በደብረ ብርሃን ከተማ አስጀምሯል፡፡
በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ ያላቸውን አቅም፣ ዕውቀት እና ጊዜ በመጠቀም የማኅበረሰብን ጉድለት ለመሙላት በሚደረገው ጥረት ላይ መሳተፍ መቻላቸው የህሊና እረፍት እንደሰጣቸው ተናግረዋል። በጎ በማድረግ ማኅበረሰብን ለማገልገል ሰው መኾን ብቻ በቂ መኾኑን ድንበር ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ ገልጸዋል፡፡
ድንበር ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ ከተለያየ የማኅበረሰብ ክፍል የተውጣጡ መኾናቸው የኢትዮጵያ እሴት የኾነውን ተቻችሎ መኖርን እንዳሳያቸው ገልጸዋል። ወጣትነትን ለተሻለ ዓላማ ማዋልም ከሁሉም ወጣቶች የሚጠበቅ በመኾኑ ኀላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት ማኅበረሰብን ማገልገል እንደሚኖርባቸውም ተጠቁሟል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋሁን ተሰማ በጎነትን ሁሉም ወጣት ሊተገብረው የሚገባ ሰብዓዊ ተግባር መኾኑን አንስተዋል። “ኢትዮጵያዊ መልካምነት የሚታይ ሳይኾን አብሮን የኖረ ነው” ያሉት ኀላፊው የበጎ ፈቃድ ተግባርን ትውልዱ በወጥነት እንዲያስቀጥለው እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ይህንን ተግባር ለማስቀጠል ወጣቶች ጉልህ ሚና እንዳላቸው አቶ ተስፋሁን ገልጸዋል፡፡
በክረምት በጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት፣ በብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ገዛኸኝ አንዳርጌ እና የተለያዩ የሥራ ኀላፊዎች ታድመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ስንታየሁ ኃይሉ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!