“በ2016/2017 ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት በዘር ለመሸፈን እየተሠራ ነው” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ

13

ባሕር ዳር: ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በ2016/2017 የምርት ዘመን 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ በዘር በመሸፈን 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሕዝብ ግንኙነት ኅላፊ አምሳሉ ጎባው ገልጸዋል።

ለመኸር የሰብል ልማቱ የሚውል 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ዩኒየኖች ገብቷል ነው ያሉት። ከዚህ ውስጥ ከ 6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሚኾነው የአፈር ማዳበሪያ ወደ አረሶአደሮች ማሳ ደርሷል ብለዋል፡፡

አርሶ አደሮች መደበኛ ኮምፖስት እንዲያመርቱ 1ሚሊዮን 231 ሺህ ሜትር ኩብ ኮምፖስት ለማዘጋጀት በእቅድ ተይዞ እንደነበርም ተገልጿል። ኾኖም ግን ማዘጋጀት የተቻለው 59 ሺህ 5 መቶ ሜትር ኩብ ነው ብለዋል ኀላፊው። የተመረተው ማዳበሪያም 1ሚሊየን 630 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ጥቅም ላይ ውሏል ነው ያሉት።

አቶ አምሳሉ ቢሮዉ ለ2017 የምርት ዘመን ወደ 5 ነጥብ 9 ሚሊዮን የሚጠጋ ምርጥ ዘር ለማምረት ከአርሶ አደሮች እና ከባለሀብቱ ጋር በመቀናጀት እየተሠራ እንደኾነም ነው የገለጹት፡፡ ክልሉ ካለበት አሁናዊ የሰላም እጦት ጋር በተያያዘ ግጭት ባለባቸዉ አካባቢዎች ተዘዋውሮ እገዛ ለማድረግ ተግዳሮት ቢኖርም በስልክ፣ በሬዲዮ እና በተለያዩ አማራጮች ለአርሶ አደሮች ምክረ ሀሳቦችን በመስጠት የግብርና ባለሙያዎች ከፍተኛ ክትትል እና ድጋፍ እያደረጉ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሮች በግብርና ባለሙያዎች በሚሰጠው ምክረ ሀሳብ መሰረት የዘር ሥራውን ከማከናወን ባለፈ በቀጣይ የአረም እና የተባይ ክትትል ሥራ በማከናወን በእቅድ የተያዘውን ምርት ውጤታማ ለማድረግ የበኩላቸዉን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) በኢትዮጵያ የቡና ምርት እና ምርታማነት እንዲረጋገጥ እየሠራ መኾኑን ገለጸ።
Next article”ማኅበረሰብን በወጣትነት ጊዜ ማገልገል መታደል ነው” ድንበር ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች