የሃይማኖት አባቶች ያላቸውን አቅም እና ተደማጭነት በመጠቀም ሰላም እንዲመጣ መሥራት እንዳለባቸው ተጠቆመ።

17

ደሴ: ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “የሃይማኖት አባቶች የሰላም ካውንስሉን ተልዕኮ ለማሳካት ሚናቸው የጎላ ነው” በሚል መሪ መልዕክት በደሴ ከተማ ከኦርቶዶክስ ሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት ተካሂዷል።

የውይይቱ ተሳታፊ የሃይማኖት አባቶች ምዕመኑ ‘ነገ ምን ይፈጠር ይሆን?’ እያለ በስጋት እየኖረ መኾኑን ገልጸዋል። መንፈሳዊ አገልግሎት ለመፈጸም የሚያስቸግር ክልላዊ ሁኔታ መፈጠሩንም ጠቅሰዋል። ቤተክርስቲያንን ተገን አድርጎ ሰላምን ለማወክ የሚንቀሳቀስ እንዳይኖር ሢሠሩ መቆየታቸውን ገልጸው ለሰላም መምጣት ቤተ ክርስቲያን እና የሃይማኖት አባቶች ኀላፊነት አለባቸው ብለዋል።

በመንግሥት በኩልም ያልተመለሱ ጉዳዮች መስተካከል እንዳለባቸው ጠቅሰው ቤተክርስቲያን ምንጊዜም ሰላምን ትሰብካለች ብለዋል። የደሴ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሸናፊ አለማየሁ መንግሥት ከሃይማኖት ወገንተኝነት የፀዳ ነው ብለዋል። ለዕኩይ ፖለቲካዊ ዓላማ ማሳኪያ ሲባል ቤተክርስቲያንን ከመንግሥት ሆድ እና ጀርባ ለማድረግ የሚሠሩ አካላት መኖራቸውንም ተናግረዋል።

ሃይማኖትን ተገን አድርገው የሚንቀሳቀሱትን ማውገዝ እና መገሰጽ እንደሚገባም ነው የስገነዘቡት። የደሴ ከተማ አሥተዳደር ቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ መንግሥት እንዲኖር እና ሃይማኖት እንዲፀና ሰላም ወሳኝ ነው ብለዋል። የሃይማኖት አባቶችም የማንም መጠቀሚያ ከመኾን ራሳቸውን እንዲጠብቁ መልዕክት አስተላልፈዋል። “ያላችሁን አቅም እና ተደማጭነት ተጠቅማችሁ ሰላም እንዲመጣ የመሥራት ኀላፊነት አለባችሁ” ብለዋል።

“የቤተክርስቲያኗን የተለያዩ ፍላጎቶች አሟልተናል፤ ለጥያቄዎቻችሁም መልስ እየሰጠን ነው፤ አሁንም አጠናክረን እንቀጥላለን” ነው ያሉት። “ሃይማኖት እና ፖለቲካ መቀላቀል የለበትም ነገር ግን አንዳንዶች የሃይማኖት ጭንብል አጥልቀው ሰላምን ለማደፍረስ ይሠራሉ” ያሉት ደግሞ የሰሜን ምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አሰፋ ቸኮል ናቸው። የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ይዟቸው የመጡ መልካም ዕሴቶች ሊከበሩ እና ሊቀጥሉ ይገባልም ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶችም ሰላምን የማስፈን እና ቤተክርስቲያንን የማስከበር ኀላፊነት አለባችሁ ነው ያሉት።

ዘጋቢ፡- መስዑድ ጀማል

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከ529 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብል በማልማት ከ17 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል” የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ
Next articleየተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) በኢትዮጵያ የቡና ምርት እና ምርታማነት እንዲረጋገጥ እየሠራ መኾኑን ገለጸ።