“ከ529 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብል በማልማት ከ17 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል” የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ

18

ባሕር ዳር: ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዘንድሮ የምርት ዘመን የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ንጉሤ ማለደ በምርት ዘመኑ ከ300 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች አዳዲስ የግብርና አሠራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር 385 ሺህ ሄክታር መሬት በሰብል ዘር መሸፈን ችለዋል፡፡ አርሶ አደሮቹ በጥቁር አፈር ማንጣፈፍ፣ አሲዳማ የእርሻ መሬቶችን በኖራ አፈር በማከም፣ በመስመር በመዝራት፣ በሜካናይዜሽንና በኩታ ገጠም የእርሻ ቴክኖሎጂ ተሳታፊ መኾን እንደቻሉም ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ 43 ሺህ ሄክታር የእርሻ መሬት ላይ የጥቁር አፈር ማንጣፈፍ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል። 20 ሺህ ሄክታር ምርት መስጠት ያቆመ አሲዳማ መሬት በኖራ በማከም ወደ ሰብል ልማት መግባቱንም አስረድተዋል፡፡ 42 ሺህ ሄክታር መሬት በትራክተር በማሳረስ 319 ሺህ ሄክታር የእርሻ መሬትን በኩታ ገጠምና በመስመር በመዝራት አርሶ አደሮቹ ምርታማነትን የሚጨምሩ የግብርና አሠራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

ጥቅም ላይ የዋሉት አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎቹ ምርታማነትን በሄክታር ከ28 ወደ 33 ኩንታል ለማሳደግ የሚያግዙ መኾናቸውን አስታውቀዋል፡፡ በምርት ዘመኑ 418 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች በወቅቱ በማሰራጨት የመኸር ሰብል ልማት ሥራውን ማሳለጥ መቻሉንና የማዳበሪያ አቅርቦቱም ካለፈው ዓመት የተሻለ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

በመኸሩ ወቅት ምርታማነትን የሚያሳድጉ የተሻሻሉ አሠራሮችን በመጠቀም 28 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር ተሸፍኗል ያሉት ደግሞ በዞኑ የጭልጋ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ደበበ ታከለ ናቸው፡፡ የጎንደር ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደር ማሩ ጌታነህ ውኃ የሚተኛበትን የጥቁር አፈር የእርሻ መሬት በዘመናዊ መንገድ በማንጣፈፍ በግማሽ ሄክታር ማሽላ ዘርተው እየተንከባከቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዓመት የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ በመቅረቡ የዘር ሥራቸውን ያለምንም ችግር ማከናወናቸውን ጠቅሰዋል። ኢዜአ እንደዘገበው የዝናብ ስርጭቱም ለወቅቱ የሰብል እድገት ተስማሚ ነው ብለዋል፡፡ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በምርት ዘመኑ ከ529 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብለ በማልማት ከ17 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅም ተገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር በዘላቂ ልማት ላይ አብሮ መሥራት የሚያስችል ውይይት አድርገናል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleየሃይማኖት አባቶች ያላቸውን አቅም እና ተደማጭነት በመጠቀም ሰላም እንዲመጣ መሥራት እንዳለባቸው ተጠቆመ።