“ከሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር በዘላቂ ልማት ላይ አብሮ መሥራት የሚያስችል ውይይት አድርገናል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

37

ባሕር ዳር: ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ከኢትዮጵያ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ በ2016 ዓ.ም ኦቻ በክልሉ ሰብዓዊ ድጋፍ ላይ የነበረውን አፈጻጸም የገመገምንበት ነበር ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በቀጣይ አብረው በሚሠሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ስለመነጋገራቸው ነው የገለጹት። ኦቻ በክልሉ ለተፈናቃይ ወገኖች እና በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች አፈጣኝ ሰብዓዊ ድጋፍ አድርጓል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ዛሬ “ከሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር በዘላቂ ልማት ላይ አብሮ መሥራት የሚያስችል ውይይት አድርገናል” ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ፖል ሃንድሊ ከርእሰ መሥተዳድሩ ጋር ያደረጉት ውይይት ያለፈውን አፈጻጸም ገምግሞ ለቀጣይ ዓመት የትኩረት መስክን መለየት ላይ ያተኮረ ነበር ብለዋል። ኦቻ ባለፈው ዓመት አማራ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ሰብዓዊ ድጋፍ አድርጓል ያሉት ዳይሬክተሩ ድርቅ እና መሰል ችግሮችን ተከትሎ ለሚፈጠር ሰብዓዊ ቀውስ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት ስለማድረጋቸውም ነው ያስረዱት።

ዳይሬክተሩ ከርእሰ መሥተዳድሩ ጋር በነበራቸው ውይይት የክልሉ መንግሥት ከአስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር በዘላቂ የልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ እንደጠየቃቸው ነው የገለጹት። በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር ከተፈታ በክልሉ ዘላቂ ልማት ላይ አብሮ ለመሥራት የሚያስችል ዝግጅት ይደረጋልም ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ በጸጥታ ችግር ውስጥ ኾኖ ያከናወነው ተግባር የሚበረታታ መኾኑ ተገለጸ።
Next article“ከ529 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብል በማልማት ከ17 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል” የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ