የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ በጸጥታ ችግር ውስጥ ኾኖ ያከናወነው ተግባር የሚበረታታ መኾኑ ተገለጸ።

58

ባሕር ዳር: ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ከተማ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።

የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ የቢሮውን የበጀት ዓመት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የጣና መቀነት ጥናት ተጠናቅቆ የጋራ መደረጉን ገልጸዋል። ለ42 ፕሮጀክቶች የአዋጪነት ጥናት ወቅታዊ የማድረግ ሥራ መሠራቱን እና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የተለያዩ ፓናል እና ፎረሞች መካሄዳቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ የሚገኙ አምራቾች በኤግዚቢሽኖች በመሳተፍ ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋዉቁ እና እንዲሸጡ መደረጉን አመልክተዋል። ለ532 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ እና 437 ቢሊዮን ብር ካፓታል ላላቸው 1 ሺህ 800 የሚጠጉ ኢንቨስተሮች በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ እና በቱሪዝም ፈቃድ መሰጠቱ ተገልጿል።

ከቀረቡ እና ከተገመገሙ 1 ሺህ 894 አምራች እና አምራች ያልኾኑ ኢንዱስትሪዎች መካከል 574 ባለሃብቶች የመሥሪያ ቦታ ማግኘታቸው ተገልጿል። በአንጻሩም ሥራ ያልጀመሩትን ውል የማቋረጥ፣ የአሠራር ጥሰት የፈጸሙትን ተጠያቂ የማድረግ ተግባር መከናወኑም ተጠቅሷል። የጸጥታ ችግር፣ የምንዛሪ እጥረት፣ የኃይል አቅርቦት እና የመሠረተ ልማት ችግር ያጋጠሙ እንቅፋቶች መኾናቸው ተጠቅሷል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት የንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ከተማ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጸጥታ ችግር ውስጥ ኾኖ ቢሮው የሠራው ሥራ የሚበረታታ መኾኑን አንስቷል። ቴክኖሎጂን በመጠቀም አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን ጥረት መደረጉ፣ ከሦስተኛ ወገን የጸዳ መሬት ለይቶ በማዘጋጀት ለኢንቨስትመንት ዝግጁ ማድረግ፣ ወደ ልማት ባልገቡ ፕሮጀክቶች ላይ እርምጃ መወሰዱ፣ ተኪ ምርት በማምረት የውጪ ምንዛሪን ለማዳን የተጀመረው ሥራ በጥንካሬ ቋሚ ኮሚቴው በግብረ መልሱ ገልጿል።

አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ግንባታ እና ማምረት ሥራ አነስተኛ መኾን፣ በግምገማ ላለፉ ኢንቨስትመንቶች መሬት ማቅረብ አለመቻል፣ በጀት ቢመደብም የተሟላው መሠረተ ልማት አነስተኛ መኾን፣ የካፒታል በጀትን ለታለመለት ዓላማ በወቅቱ አለመጠቀም፣ ለኦዲት ግኝቶች እና ለቋሚ ኮሚቴው አስተያየት ምላሽ አለመሰጠቱ በውስንነት የተነሳ ሲኾን በቀጣይም ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራባቸው አስተያየት ተሰጥቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበምዕራብ ጎንደር ዞን ከ20 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሁለት ተንጠልጣይ ድልድዮች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸው ተገለጸ።
Next article“ከሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር በዘላቂ ልማት ላይ አብሮ መሥራት የሚያስችል ውይይት አድርገናል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ