
ገንዳ ውኃ: ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ እና መተማ ወረዳ ከ20 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሁለት የእግረኛ ተንጠልጣይ ድልድዮች ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸውን የዞኑ መንገድ መምሪያ ኀላፊ ዓባይነህ ወረታ ተናግረዋል።
የእግረኛ ተንጠልጣይ ድልድዮች በክልሉ መንግሥት እና ሄልቬታስ ኢትዮጵያ ከተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት በተገኘ 10 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ወጭ መገንባታቸውን ነው ኀላፊው የገለጹት። መምሪያ ኀላፊው እንደገለጹት አንደኛው በቋራ ወረዳ አብታጋሆ ቀበሌ የሚገኘው የሻሆ ወንዝ ተንጠልጣይ ድልድይ ሲኾን በ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጭ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል። 80 ሜትር ርዝመት ያለው ይህ ድልድይ አምስት ቀበሌዎችን የሚያገናኝ ነው ብለዋል።
ሁለተኛው ደግሞ በመተማ ወረዳ መቃ ቀበሌ የሚገኘው የገንዳ ውኃ ወንዝ ተንጠልጣይ ድልድይ ነው። ይህ 100 ሜትር ርዝመት ሲኖረው በ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ወጭ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል። አራት ቀበሌዎችንም ያገናኛል ተብሏል። አካባቢው ከእንስሳት እርባታ ባሻገር እንደ ሰሊጥ ፣ አኩሪ አተር፣ ጥጥ፣ ማሽላ እና ሌሎች የቅባት ሰብሎች እንደሚመረቱበት የገለጹት አቶ ዓባይነህ አርሶ አደሮች ምርታቸውን በተሻለ ዋጋ ሽጠው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዳይኾኑ ድልድዮቹ ባለመኖራቸው እንቅፋት ኾነው መቆየታቸውን ተናግረዋል።
አሁን ላይ የተገነቡት ተንጠልጣይ ድልድዮች በነዋሪዎች ላይ ይደርስ የነበረውን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመፍታት የሚያስችል ነው ብለዋል። እንደ ክልል የጸጥታ መደፍረስ ቢያጋጥምም ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታውን ተቋቁሞ የነዋሪዎችን የረጅም ጊዜ ጥያቄ መፍታት ተችሏል ነው ያሉት።
ሁለቱም የእግረኛ ተንጠልጣይ ድልድዮች በ2016 በጀት ዓመት በዞኑ በዕቅድ ተይዘው በታለመላቸው ጊዜ መጠናቀቃቸው ነው የተገለጸው። ተንጠልጣይ ድልድዮች በዘላቂነት እንዲያገለግሉ ኀብረተሰቡ በኀላፊነት ስሜት ሊጠብቃቸው እንደሚገባም መምሪያ ኀላፊው አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!