
ባሕር ዳር: ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ እና የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው በክልሉ ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው ክልሉ ከነበረበት የጸጥታ ችግር እየወጣ የተሻለ ሰላም ላይ መኾኑን ተናግረዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ የጸጥታ ኀይል ከሕዝቡ ጋር በሠራው ሥራ ክልሉ ተጋርጦበት ከነበረው የመፍረስ አደጋ መውጣቱን ነው ያስታወሱት። የጸጥታ ችግሩ ከተከሰተበት ጊዜ አንጻር ሲታይ የክልሉ ሰላም ትልቅ መሻሻል ውስጥ መኾኑንም አስታውቀዋል።
ከክልል ጀምሮ እስከታችኛው ያለው አብዛኛው የመንግሥት መዋቅር መደበኛ ሥራውን እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። በምጣኔ ሃብት ተጠቃሚ የኾነ ማኅበረሰብ እና ተወዳዳሪ የኾነ ክልል እንዲኾን ለማድረግ ሥራዎችን እየተሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል። ነገር ግን የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚሠሩ ሥራዎች እንቅፋት የኾኑ ችግሮች መኖራቸውን ነው የተናገሩት።
በክልሉ ሰላማዊ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ አለመኖሩንም ተናግረዋል። አርሶ አደሮች በሙሉ አቅማቸው እንዳይሠሩ የሚረብሹ ችግሮች መኖራቸውንም አስረድተዋል። በክልሉ የተሻሻለ ሰላም አለ ስንል ሙሉ ለሙሉ ሰላም ተረጋግጧል ማለታችን አይደለም ነው ያሉት። የክልሉን የጸጥታ መዋቅር በማደራጀት እና በመገንባት በራሱ አቅም የክልሉን ሰላም ለመጠበቅ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል። ክልሉ በፈተና ውስጥም ኾኖ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን እያሳካ መኾኑንም አብራርተዋል።
ግጭቱ ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ የአማራ ክልል ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን ማድረጉን አንስተዋል። በሰላም ጥሪዎች ትልቅ ለውጥ መገኘቱን እና በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖች ወደ ሰላም መግባታቸውንም ተናግረዋል። የሰላም ጥሪዎች እና አማራጮች ዛሬም ድረስ መቀጠላቸውን አስታውቀዋል።
የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለመመለስ ከሕዝብ ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ መንግሥትን እና የታጠቁ ኀይሎችን ለማገናኘት አመቻች የሰላም ካውንስል መቋቋሙን ያስታወሱት ኀላፊው በአማራ ክልል የተቋቋመው የሰላም ካውንስል የመንግሥትንም ኾነ በጫካ የሚገኙ ወንድሞችን ሃሳብ የተሸከመ አለመኾኑንም ገልጸዋል።
መንግሥት ከሰላም የሚገኘውን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅሞችን ታሳቢ በማድረግ ለድርድር ዝግጁነቱን መግለጹንም አቶ ደሳለኝ አንስተዋል። ጫካ የሚገኙ ወንድሞች ለድርድር ጆሮ ሰጥተው የሚመጡ ከኾነ በየትኛውም አደራዳሪ ወገን ለመደራደር ግልጽ የኾነ አቋም መያዙንም ገልጸዋል። የሰላም ካውንሰሉ ጫካ የገቡ ወንድሞች ጥያቄዎችን ይዘው ወደ ድርድር እንዲገቡ ጥሪ እያቀረቡ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የሰላም ካውንስሉ ያቀረበው ጥሪ እና የክልሉ መንግሥት ያሳየው ዝግጁነት ሰፊ የሕዝብ ይሁንታ ያገኘ መኾኑንም ገልጸዋል።
የሰላም ካውንስሉ አባላት ከየትኛውም ወገን የፖለቲካ አስተሳሰብ ገለልተኛ የኾኑ፣ የአማራን እና የመላው ኢትዮጵያውያንን የሰላም ፍላጎት የያዙ፣ ግጭት እንዲቆም የሚፈልጉ ናቸው ብለን እናምናለን ነው ያሉት። የሰላም ካውንስሉ አባላት የመጨረሻ ግባቸው ሰላምን ማምጣት መኾኑንም አንስተዋል። ለድርድሩ እና ለሰላም ጥሪው ልባችንን መክፈት አለብን፤ የሕዝብ ስቃይ ሊቆም ይገባልም ብለዋል።
በርካታ ኀይሎች ለሰላም ጥሪው እና ለድርድሩ መልካም ይሁንታ አላቸው ያሉት ኀላፊው አሁንም ለሰላም ድርድሩ ልብን ከፍቶ ያለመቀበል እና ያለማመን ጥርጣሬዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል። መንግሥት የሰላም ውይይቱን እና ድርድሩን የፈቀደው ለፖለቲካ ትርፍ ሳይኾን ለአማራ ሕዝብ ሰላም እና እረፈትን ለመስጠት ነው ብለዋል።
ያለፈው የሕዝብ እልቂት እና ስቃይ የማይገባቸው ኀይሎች መኖራቸውን የተናገሩት ኀላፊው የሰላም አማራጭ በአንድ ወገን ብቻ የሚመጣ አለመኾኑንም ተናግረዋል። ሰላም የሕዝብ እና የመንግሥት ፍላጎት ቢኾንም ከሰላም ያፈነገጡ ኀይሎች ላይ የሕግ ማስከበር ለመውሰድ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።
የሕዝብን ዓላማ እና ፍላጎት ገበያ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ያለው ቡድን አሁንም በሕዝብ ላይ አረመኔያዊ ድርጊቱን እንደቀጠለ ነው ብለዋል። የታጠቁ ኀይሎች ከአሁን በፊት በጎንደር ቀጣና ደምቢያ አካባቢ ስለ ሰላም እና ስለ ውይይት የሄዱ ቀሳውስትን፣ ሼሆችን እና የሀገር ሽማግሌዎችን ይዘው ከሕዝብ እሴት ባፈነገጠ መልኩ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አስከፍለው መልቀቃቸውን አስታውሰዋል።
ሞት ይበቃል ብለው ለድርድር እና ለውይይት ሲቀሰቅሱ የነበሩ አባት በደብረማርቆስ ከተማ መገደላቸውንም ተናግረዋል። ሰላም የማይናፍቃቸው እና ከሰላም ጋር የተጣሉ ቡድኖች ከሰሞኑ ደግሞ በሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ ሜጫ ወረዳ ገርጨጭ ላይ ንጹሐንን ገድለዋል ነው ያሉት።
ማኅበራዊ ሕይወታቸውን ከውነው የተመለሱ በሕዝብ ዘንድ ተሰሚነት ያላቸው፣ የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌላቸው 15 ሰዎችን ገበያ ላይ በማንበርከክ መቅጣታቸውን ገልጸዋል። በግፍ የተቀጡት ንጹሐን የተከበሩ እና አንቱ የተባሉ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። ከተሰቃዩት ቄስ፣ ሽማግሌ እና ሴቶች መካከል አራቱ በግፍ ተገድለዋል ነው ያሉት። የወረዳው ቤተ ክህነት ኀላፊ የነበሩ መርጌታ ግሩም፣ አዛነ ደምሴ፣ አስማማው አቤ የተባሉ የሀገር ሽማግሌ እና ወይዘሮ የኔአየሁ የተባሉ እናት በግፍ ተረሽነዋል፣ ቀሪዎቹ የት እንዳሉ አይታወቅም ነው ያሉት ኀላፊው።
የአጥፊ ቡድን አባላት እና መሪዎች በሰላም አማራጮች ላይ ውኃ እየቸለሱ ኅብረተሰቡ ያየው የሰላም ተስፋ እውን እንዳይኾን እያደረጉ ነው ብለዋል። የመጀመሪያ እና የመጨረሻ አማራጭ ሰላም ነው ያሉት ኀላፊው ለሀገር የሚጠቅም የሰላም ሃሳብ ይዞ በመቅረብ መደራደር ይገባል ነው ያሉት። በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር እያጠፋ ያለው በአብሮነት የሚያምነውን እና በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረውን የአማራ ክልልን ሕዝብ ነው ብለዋል።
በታሪካዊ ጠላቶች የገንዘብ እና የመሳሪያ ድጋፍ ወንድማቸውን የሚገድሉ አካላት መኖራቸውንም ገልጸዋል። የራሱን ሕዝብ የሚገድልን አርበኛ ማለት እንደማይገባም አስገንዝበዋል። የአማራ ሕዝብ ዝቅ እንዲል የሚያደርጉ ኀይሎች መኖራቸውንም ገልጸዋል። በየቀኑ ንጹሐንን የሚረሽኑ ቡድኖች አሉ ነው ያሉት። የክልሉ ሕዝብ ለተጀመረው የሕግ ማስከበር ሥራ አቅም ኾኖ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ መንግሥት ለሰላም አማራጭ እና ለሰላም ካውንስሉ ያለው አቋም ዛሬም ቢኾን የጸና ነው ብለዋል። ለሰላም እና ለድርድር የሚመጡ ኀይሎችን አንድ እርምጃ ሄደው እንደሚቀበሉም አስታውቀዋል። አንዳንድ አካላት ግን የቀረበውን ሃሳብ ለጊዜ መግዣ እና ለዘረፋ እየተጠቀሙበት ባሉ አካላት ላይ የሕግ ማስከበር እርምጃ መውሰድ ይገባልም ብለዋል። ግድያን፣ ዘረፋን እና እገታን ለማስቆም ሕግ የማስከበር ሥራን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።
ሕዝብ የግፍ ግድያ እና ዘረፋ በቃኝ በማለት እያሳየ ያለውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!