በምዕራብ ጎንደር ዞን የወባ ሥርጭት መጨመሩን የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ።

15

ገንዳ ውኃ: ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሐምሌ ወር በዞኑ ከፍተኛ የወባ ስርጭ መከሰቱን የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ የወባ እና ቬክተር ወለድ በሽታዎች መከላከል ቡድን መሪ አቶ ወርቁ መንግሥቴ ገልጸዋል። የወባ በሽታ በዞኑ ባሉ ሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች እንዲሁም በሱዳን የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ላይ መከሰቱንም ተናግረዋል። የወባ ሥርጭቱ በተለይም በመተማ፣ ቋራ እና ምዕራብ አርማጭኾ ወረዳዎች በስፋት መከሠቱን አስረድተዋል።

በበጀት ዓመቱ የወባ በሽታ ሥርጭትን እስከ 50 በመቶ ለመቀነስ ቢታቀድም የሥርጭት መጠኑ ግን መጨመሩን ነው ቡድን መሪው የተናገሩት። በ2016 በጀት ዓመት በዞኑ ምርመራ ካደረጉ ከ400 ሺህ በላይ ዜጎች 127 ሺህ 500 የሚኾኑት በወባ መያዛቸው ተገልጿል። በሐምሌ ወር የመጀመሪያው ሳምንት ከተመረመሩ 9ሺህ 5 መቶ ግለሠቦች መካከል 3 ሺህ 2 መቶ 93 የወባ በሽታ ተገኝቶባቸዋል ብለዋል አቶ ወርቁ። አሁን ላይ ያለው የወባ በሽታ የሥርጭት መጠኑ 31 በመቶ መድረሱንም ጠቁመዋል ።

ቡድን መሪው እንደገለጹት የወባ በሽታውን ለመከላከል ቆሻሻዎችን የማቃጠል እና የማዳፈን ፣ ውኃ ያቆሩ አካባቢዎችን የማፋሰስ እና ሌሎች የአካባቢ ቁጥጥር ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። በባለሀብቶች የእርሻ ልማት ጣቢያዎች የሕክምና አገልግሎት አለመኖር፣ የወባ መድኃኒት ግብዓት እጥረት መከሰቱ እንዲሁም የኬሚካል ርጭት እና የአጎበር ሥርጭት አለመደረጉ በሽታውን ለመቀነስ እንቅፋት እንደፈጠረም ገልጸዋል።

አሁን ላይ በዞኑ አዳኝ አገር ጫቆ ወረዳ በ6 ቀበሌዎች የወባ መከላከያ ኬሚካል ርጭት እየተደረገ ነው ብለዋል አቶ ወርቁ። በሌሎች አካባቢዎች የአጎበር ሥርጭት እና የኬሚካል ርጭት እንዲደረግ ቬክተር ሊንክ ኢትዮጵያ ከተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት ጋር እየተነጋርን ነው ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰሜን ወሎ ዞን በሀራ ከተማ አሥተዳደር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ተካሄደ።
Next article“መንግሥት የሰላም ውይይቱን እና ድርድሩን የፈቀደው ለፖለቲካ ትርፍ ሳይኾን ለአማራ ሕዝብ ሰላም ለመስጠት ነው” አቶ ደሳለኝ ጣሰው