”የከተማ አገልግሎት አሠጣጥ ከደላላ ጣልቃ ገብነት ነጻ መኾን አለበት” የንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ከተማ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ

47

ባሕር ዳር: ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ለአማራ ክልል ምክር ቤት የንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ከተማ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል።

የቢሮው ምክትል ኀላፊ ሱሌይማን እሸቱ ባቀረቡት ሪፖርት መሬትን በማዘጋጀት እና ማስተላለፍ በኩል ከዕቅዱ ግማሹን ማከናወኑን ገልጸው መሬት የሚተላለፍላቸው አልሚዎች ወደ ሥራ አለመግባት ችግር እንደታየባቸው ተናግረዋል። መሬታቸው ተነጥቆ ወደ መሬት ባንክ የተመለሰ መኖሩንም ተናግረዋል።
ሕዝብን እና መሪዎችን አሳትፎ የከተማ ፕላን ማዘጋጀትም ላይ ውስንነት እንደነበርም ጠቅሰዋል።

ከዕቅዱ 43 በመቶ አፈጻጸም ያለው የቤቶች ልማት መኖሩን እና ሪል ስቴቶች እና ለዝቅተኛ ነዋሪዎች ቤት መሠራቱም ተነስቷል። የመንግሥት ቤቶችን በመረጃ ቋት ለማስገባት 30 ሺህ ታቅዶ በኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት 5 ሺህ 400 ብቻ መከናወኑን ገልጸዋል።

የከተማ መሠረተ ልማትን ለመፈጸም 898 ሚሊዮን ብር በመመደብ ካለፈው ዓመት የተንከባለሉትን ጨምሮ 523 ፕሮጀክቶች እየተፈጸሙ መኾኑ በሪፖርቱ ተገልጿል። ከዩ አይ አይ ዲፒ ፕሮጀክት ውጪም 377 ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ገብተው በመጠናቀቅ ሂደት ላይ መኾናቸውን አስረድተዋል።

ከተሞችን ጽዱ እና ውብ ለማድረግ አረንጓዴ ቦታዎችን ማልማት፣ ቆሻሻን ማስወገድ እና የካርታ ዝግጅት መሠራቱን ጠቁመዋል። የከተማ ምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት ፕሮግራም በ18 ከተሞች በውጤታማነት እየተፈጸመ እንደኾነም በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

በሁሉም የከተማ ልማት ዘርፍ ሥራዎች የሴቶች ድርሻ እስካሁን 30 በመቶ እንደደረሰ ተጠቅሷል። የሥራ ዕድል ፈጠራ በጸጥታ ችግር ምክንያት ከታቀደው ግማሽ ያክሉ ብቻ መከናወኑን አቶ ሱለይማን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ አጋጥመዋል ተብለው ከተጠቀሱት ችግሮች መካከል፦
👉 የመሬት ወረራ እና ሕገ ወጥ ግንባታ፣
👉 በብልሹ አሠራር ላይ አስተማሪ እርምጃ አለመውሰድ
👉 የአገልግሎት አሰጣጥ ድክመት ዋናዎቹ ናቸው።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት አስተያየቶች እና ጥያቄዎችን አንስተዋል።
👉 አገልግሎት የሚገኘው በእጅ መንሻ እና በደላላ መኾኑ እንደቀጠለ ነው፣ ቢሮውም ሁልጊዜ ያነሳዋል ግን መቅረፍ አልቻለም። የጸረ ሌብነት ትግሉ ከመድረክ ንግግር ያለፈ አልኾነም ብለዋል፡፡
👉 ሁሉም የዞኒንግ ለውጥ ጥያቄዎች ችግር ያለባቸው ስለማይኾኑ እየተመረመሩ ቢስተናገዱ ሲሉም አንስተዋል፡፡
👉ለልማት ከይዞታቸው የሚፈናቀሉ አርሶ አደሮች የካሳ እና የመልሶ ማቋቋም ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠውም ነው ያሳሰቡት፡፡
👉 የቤት መሥሪያ ቦታ ለማግኘት የተደራጀው ሕዝብ ውጣ ውረድ የበዛበት እና እስካሁንም ያላገኘው በርካታ መኾኑን በመግለጽ መስተካከል እንደሚገባው ነው ያስረዱት።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በአፋጣኝ እንዲሻሻሉ ካነሷቸው ሃሳቦች መካከል፡-
👉 በየደረጃው ያሉ የሥራ መደቦችን በሠራተኛው በመሸፈን የአገልግሎት አሰጣጡ እንዲሻሻል ማድረግ
👉 ሕዝብን ያማረረው የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አሥተዳደር ችግርን መፍትሔ መስጠት
👉 ከመብራት፣ ውኃ፣ ቴሌ እና መሰል ጉዳዮች ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ችግሮቹን መፍታት
👉 የከተማ አሥተዳደሮች የፋይናንስ አጠቃቀም ኦዲት ዝቅተኛነት ታይቶ ከፍ እንዲደረግ መሥራት
👉 ሕገ ወጥ ይዞታን ለማስተካከል የተሠራው ሥራ አነስተኛ በመኾኑ በቀጣይ ትኩረት የሚሻ መኾኑም ተነስቷል።
👉 በልማት ከይዞታቸው ለሚነሱ ባለይዞታዎች የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመኾኑ እንዲፈተሽ እና
👉 ጽዱ ከተሞችን በመፍጠር እና በቆሻሻ አወጋገድ የሚታይ ውስንነት ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊሠራባቸው እና ሊሻሻሉ እንደሚገባ ተመላክቷል።
ቋሚ ኮሚቴው የተሻለ አፈጻጸም እና በጥንካሬ ያያቸውን ተግባራትንም ጠቁሟል፡-
👉 የከንቲባ ችሎት መጀመር
👉 ከጸጥታ ችግሩ ጋር በተያያዘ የመሬት ወረራ የፈጸሙ መሪዎች እና ሙያተኞች ላይ እርምጃ መወሰዱ
👉 ለአረንጓዴ ቦታዎች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መሠራቱ በጥንካሬ ከተመላከቱት መካከል ናቸው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበ2017 በጀት ዓመት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ወደ 4 ነጥብ 52 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑ ተገለጸ፡፡
Next articleበሰሜን ወሎ ዞን በሀራ ከተማ አሥተዳደር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ተካሄደ።