
ባሕር ዳር: ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሃና አርአያሥላሴ እንደተናገሩት ኮሚሽኑ በ2017 በጀት ዓመት አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃዶችን በመስጠት ከውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ አቅዶ እየሠራ ነው፡፡
እንደ ኮሚሽነሯ ገለጻ በ2017 በጀት ዓመት 386 አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት እና ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት 4 ነጥብ 52 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡
ወይዘሮ ሃና እንደተናገሩት የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታን ማሻሻል፣ በ2016 በጀት ዓመት የወጡ አዳዲስ ሕጎችን ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ማስገባት፣ የሎጂስቲክስ እና የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ሥርዓት ማሻሻያዎችን ማድረግ እና የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ሥራን ማጠናከር የሚያስችል አዲስ የኢንቨስትመንት ስትራቴጂ ተቀርጿል፡፡
ወይዘሮ ሃና እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ የኮሚሽኑ አንዱ እና ትልቁ ሥራ የኢንቨስትመንት እና የፕሮሞሽን ሥራ ላይ ለሚገኙት ኢንቨስተሮች የተሻለ አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ ኢፕድ እንደዘገበው የተሻለ አገልግሎት መስጠት ሲቻል ደግሞ ሌሎች ኢንቨስተሮችን መሳብ ያስችላል ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!