የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ ለዘላቂ የሥራ ዕድል ፈጠራ በትኩረት እንዲሠራ ተጠየቀ።

46

ባሕር ዳር: ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ምክር ቤት የንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ከተማ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮን የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ዝርዝር ሪፖርትን አድምጧል። የቢሮው ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) ባቀረቡት ሪፖርት በበጀት ዓመቱ ከ980 ሺህ በላይ የሥራ ዕድል መፈጠሩን እና ይህም የእቅዱ 80 በመቶ መኾኑን ገልጸዋል።

126 የሀገር ውስጥ ሥራና ሠራተኛን አገናኝ እና የውጪ ሀገር የሥራ ስምሪት ኤጀንሲዎች ቁጥጥር መደረጉንም ገልጸዋል። ለውጪ ሀገር የሥራ ዕድልም የቅድመ ጉዞ ሥልጠና መብት እና ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲሄዱ በማድረግም ሥራ መሠራቱን በሪፖርቱ ተጠቅሷል። በሀገር ውስጥ እና በውጪ ሥራና ሠራተኛን ለማገናኘት ኤጀንሲዎችን በመከታተል መሠራቱ ተገልጿል። የዜጎችን ደኅንነት የጠበቀ የውጪ ሀገር የሥራ ስምሪት ከእቅድ በላይ መፈጸሙን ዶክተር ስቡህ ተናግረዋል።

ለአንቀሳቃሾች እና ኢንተርፕራይዞች የሀገር ውስጥ ገበያ ለማስተሳሰር ታቅዶ 70 በመቶ መከናወኑን የጠቀሱት የቢሮው ኀላፊው ከውጪ ሀገር ገበያ ትስስርም ለ615 አንቀሳቃሾች 659 ሺህ በላይ የአሜሪካን ዶላር መገኘቱንጠቁመዋል። አፈጻጸሙም የዕቅዱን 48 በመቶ ብቻ መኾኑን አመላክተዋል።

ከ31 ሺህ በላይ ለኾኑ ኢንተርፕራይዞች ለማቅረብ ከታቀደው 3 ቢሊዮን 310 ሚሊዮን ብር ብድር ውስጥ 1 ቢሊዮን 130 ሚሊዮን ብር ለ14 ሺህ አንቀሳቃሾች መቅረቡ ተመላክቷል በዕድገት ተኮር ዘርፎች ላይም የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ መደረጉ፣ አዲስ ኢንተርፕራይዞችን የመፍጠር እና ነባሮቹን የማሸጋገር ሥራ መሠራቱን ዶክተር ስቡህ ገልጸዋል።

በመንግሥት እና በግል ኮሌጆች ሠልጣኞችን ተቀብሎ ማሠልጠኑ በ40 በመቶ ዝቅ ብሎ መፈጸሙ ተጠቅሷል። አጫጭር ሥልጠናም ለ480 ሺህ ሠልጣኞች መሰጠቱን ይህም ከእቅዱ ግማሽ ያክል መኾኑ ተመላክቷል። የጸጥታ ችግር፣ የኤሌክትሪክ ኀይል መቆራረጥ፣ የኢንተርኔት መዘጋት እና የግብዓት እጥረት ማነቆዎች እንደነበሩ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

በባለሃብቶች እና በመሪዎች የተያዘውን ሼድ እና ኮንቴይነሮችን በፍጥነት በማስመለስ ማስተካከል እንደሚገባ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራው የተዓማኒነት እና የዘላቂነት ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው፣ ተፈጠረ የተባለው የሥራ ዕድልም የሚከፈለው ደመወዝ በጣም አነስተኛ በመኾኑ በልቶ የሚያሳድር አለመኾኑ፣ በተቋሙ ውስጥ ለሠሩት የማበረታቻ እና ላልሠሩት የተጠያቂነት አሠራር እንዲኖር አስተያየቶች ተሰጥተዋል።

ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ማብራሪያ የተሰጠ ሲኾን የቋሚ ኮሚቴው ግብረ መልስም ቀርቧል። የቋሚ ኮሚቴው ሠብሣቢ በላይ ዘለቀ በኮሚቴው ግብረ መልስ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በኢንተርፕራይዞች ምስረታ፣ በሀገር ውስጥ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የውጪ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለየደረጃው ተቋማት የአቅም ግንባታ ሥራ መሠራቱ እንዲሁም ለዘርፈ ብዙ ተግባራት የተሰጠው ትኩረት በጥንካሬ እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል።

በቀጣይ እንዲስተካከሉ ከተጠቆሙት መካከል ደግሞ የኢንተርፕራይዞችን የፋይናንስ ችግር በመቅረፍ በኩል ውስንነት መኖሩ፣ የተገነቡ ሸዶችን በፍጥነት ለተጠቃሚዎች አለማስተላለፍ፣ በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ ሸዶች እና ኮንቴይነሮችን አለማስመለስ፣ በአምራች ዘርፍ ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የማሽነሪ አቅርቦት አነስተኛ መኾኑ እና በኦዲት ሪፖርት የተገኘን ጉድለት አለማስመለስ የሚሉት ናቸው።

በቀጣይም ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲስተካከሉ አስተያየት ተሰጥቷል። ሁሉም ሂደቶች መዳረሻቸው የሥራ ዕድል ፈጠራ እና በልቶ ማደር ስለኾነ ግቡ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ አስተያየት ሰጪዎች አጽዕኖት ሰጥተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደቡብ ወሎ ዞን 329 አዲስ የመጠጥ ውኃ ተቋማት ተገንብተው ለተጠቃሚዎች ክፍት ኾኑ፡፡
Next articleበ2017 በጀት ዓመት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ወደ 4 ነጥብ 52 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑ ተገለጸ፡፡