በደቡብ ወሎ ዞን 329 አዲስ የመጠጥ ውኃ ተቋማት ተገንብተው ለተጠቃሚዎች ክፍት ኾኑ፡፡

12

ባሕር ዳር: ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ አስቴር ሹሜ የንጹህ መጠጥ ውኃ ለማግኘት ረጅም ርቀት በእግር ይጓዙ እንደነበር ይናገራሉ።

አሁን ላይ በአካባቢያቸው የውኃ ተቋም በመገንባቱ ችግራቸው መፈታቱን ገልጸዋል። ለወይዘሮ አስቴር እና መሰሎቻቸው ችግራቸው በመፈታቱ በአካባቢያቸው ትልቅ ደስታን ፈጥሯል፡፡ በውኃ ተቋማት ብልሽት ለንጹህ መጠጥ ውኃ ችግር ተዳርገው እንደቆዩ ያስታወሱት ሌላዋ የደሴ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ አረጋሽ ይመር የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግሩ የከፋ እንደነበር ነው ያስታወሱት።

ለውኃ ተቋሙ ጥገና ተደርጎ በአሁኑ ወቅት መልሶ አገልግሎት በመጀመሩ ችግራቸው ተፈትቶ ንጽህናው የተጠበቀ ውኃ መልሰው ማግኘታቸውን ተናግረዋል። በደቡብ ወሎ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አዳዲስ የውኃ ተቋማትን በመገንባት እና የተበላሹትን በመጠገን መልሰው ለአገልግሎት እንዲበቁ ሢሠራ ቆይቷል፡፡

በዚህም የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ሽፋንን ለማሳደግ በተደረገ ጥረት 329 አዲስ የመጠጥ ውኃ ተቋማት መገንባታቸውን የደቡብ ወሎ ዞን ውኃ እና ኢነርጂ መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው ጽጌ ተናግረዋል። በተገነቡት የውኃ ተቋማት ከ123 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች የንጹህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በተለያዩ ምክንያቶች ተበላሽተው የነበሩ 2 ሺህ 800 የውኃ ተቋማትን በመጠገን ለአገልግሎት መብቃታቸውን አስረድተዋል። ለአዳዲስ ግንባታ እና ለተበላሹት ጥገና ከ182 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን የጠቀሱት ኀላፊው ኅብረተሰቡ ለጥገና እና ለግንባታ ሥራው በገንዘብ እና በጉልበቱ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብራርተዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ በደቡብ ወሎ ዞን በበጀት ዓመቱ በተከናወኑ ሥራዎች የመጠጥ ውኃ ሽፋንን ከነበረበት ከ65 ነጥብ 9 በመቶ ወደ 68 ነጥብ 4 በመቶ ማሳደግ መቻሉ ተመላክቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አማራጭ የለም እየጠላነውም እንኖራለን፤ ከመሞት መሰንበት ይሻላል በሚል” ተፈናቃይ እናት
Next articleየአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ ለዘላቂ የሥራ ዕድል ፈጠራ በትኩረት እንዲሠራ ተጠየቀ።