“አማራጭ የለም እየጠላነውም እንኖራለን፤ ከመሞት መሰንበት ይሻላል በሚል” ተፈናቃይ እናት

83

ባሕር ዳር: ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከሞቀ ቤት ወጥተው በሸራ ውስጥ ጎጆ ከቀለሱ ዓመታት ተቆጥረዋል፤ የቤታቸው ጓዳው ናፍቋቸዋል፤ ጓሮው ውል ይልባቸዋል፤ ከላሞቻቸው ወተት፣ ከበሬዎቻቸው እሸት መቅመስ ካቆሙ ጊዜያት አልፈዋል፡፡ እልል ተብሎ ከተዳሩበት፣ ወግና ማዕረግ ካዩበት፣ ልጆች ወልደው ካሳደጉበት፣ አሳድገው ወግ ማዕረግ ካሳዩበት ቀዬ ወጥተው በችግር መኖር ከጀመሩ ጊዜያት ነጉደዋል፡፡

ጠላውን ጠምቀው፣ ጠጁን ጥለው፣ እንጀራውን ጋግረው እንግዳ የሚቀበሉበት፣ የመሸበት የሚያሳድሩበት፣ የደከመውን የሚያሳርፉበት፣ ስንቅ አስይዘው የሚሸኙበት ቤታቸው ከፈረሰ ቆይቷል፡፡ ልጆቻቸው ተወልደው ካደጉበት ርቀዋል፤ ጋራና ሸንተረሩን ናፍቀዋል፤ ልጆች ከጓደኞቻቸው ጋር የሚጫወቱበት፣ መልካሙን ጊዜ የሚያሳልፉበት የቀያቸው ሜዳ እንደ ሰው ውል ይላቸዋል፡፡

ሁሉን ከታች ከኾነች የሞቀች ቤታቸው ወጥተው በበጋ ወበቁ ይጠብሳቸዋል፤ በክረምት ብርዱ ይገርፋቸዋል፤ ዝናብ በላያቸው ላይ ይፈስሳል፤ ሌቱ መቸ በነጋልን፣ መቼ ጀምበር በጠለቀች እያሉ በድቅድቅ ጨለማ ሲጨነቁ ያድራሉ፡፡ ሰው አይብኝ ብለው ልጆቻቸውን የሚያሳድጉ እናቶች ልጆቻቸውን ዝናብ እየመታባቸው፤ ረሃብ እየገረፋቸው፣ መራባቸውን ሰው እያየባቸው፣ እንባቸውን ሲያፈስሱ ውለው ያድራሉ፡፡

ከራስ በላይ ለሰው የሚተርፉት፣ ለተቸገረ የሚደርሱት ደጋጎቹ በደል ሳይገኝባቸው፣ እንደበደለኛ ተቆጥረው፣ መልካም ባደረጉ ክፉ ተመልሶላቸው በችግር ውስጥ እንዲኖሩ ተገድደዋል፡፡ ማደሪያቸው ደሳሳ፣ ቀለባቸው አናሳ ኾኖባቸዋል፡፡ ወደ ናፈቁት ቀያቸው ይመለሱ ዘንድ አብዝተው ናፍቀዋል፡፡

ከቀያቸው ርቀው በመጠለያ የሚኖሩ ወገኖች ከክረምቱ መግባት ጋር ተያይዞ የጎርፍ አደጋ ያሰጋቸዋል፡፡ የጤና ችግርም ያሳስባቸዋል፡፡ የአራት ልጆች እናት ናቸው፡፡ ልጆቻቸውን ሰው አይይብኝ ብለው ሸሽገው ማሳደግን የሚሹ እናት፡፡ ዳሩ ተገፉና እርሳቸውም ልጆቻቸውም ከሰው ፊት ወደቁ፡፡ የሕወሓት ወራሪዎች ባደረሱባቸው ጥቃት ቀያቸውን ለቀው ለመኖር ተገድደዋል፡፡ አሁን ከልጆቻቸው ጋር በቆቦ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ በክረምት ከቤት መራቅ፣ ልጆች ይዞ ባልተመቸ ሥፍራ መኖር ሕይወትን አክብዶባቸዋል፡፡ አሁን ስለሚኖሩበት ሕይወት ሲናገሩ፡-

“አኗኗራችን በጣም ከባድ ነው፤ የሚያስጠላም ነው፣ ግን አማራጭ የለም እየጠላነውም እንኖራለን፣ ከመሞት መሰንበት ይሻላል በሚል፣ ነፍሳችንን ለማትረፍ ስንል ወጣን፡፡ ልጆች ይዞ ከቤት ርቆ መኖር የሚያስቸግር አኗኗር ነው፡፡ ብዙ ነገር የለመዱ ልጆች ብዙ ነገር አጥተው፣ እኛም እንደ ልብ በማንቀሳቀስበት ሁኔታ ውስጥ ኾነን መኖር አስቸጋሪ ነው” ይላሉ፡፡

እንደ እርሳቸው ሁሉ ሌሎች እናቶችም የልጆቻቸውን ለቅሶ ችለው፣ የልጆቻቸውን መከፋት እያዩ ይኖራሉ፡፡ ቀን ወጥቶ ደስታ እስኪመለስ ድረስ ይጠባበቃሉ፡፡ “ ልጆቼን መቼ ይገሉብኝ ይኾን እያልኩ ከምሳቀቅ ሰላም ወዳለበት አካባቢ ርቆ መቀመጥን መርጫለሁ፡፡ በቤታችን ሳለን የምንኖረው ኑሮ እና የአሁኑ ኑሮ ሲነጻጸር ያሳዝናል፤ ልጆቼ ትምህርታቸውን አቋርጠዋል፤ ወደቤታችን እንሂድ እያሉ ያለቅሳሉ፣ እኔም እነርሱን ሳይ አለቅሳለሁ፤ በጣም ከባድ ነው” ነው ያሉት፡፡

ከክረምቱ ጋር መጠለያውም ለመኖር እንደማይመች ነው የተናገሩት፡፡ ልጆች ይዞ ዝናብ ባለበት፣ ጎርፍ በሚመጣበት ቦታ መኖር አይቻልም ነው ያሉት፡፡ የራያ ቆቦ አካባቢ ነዋሪዎች ምግብ እያወጡ እየሰጡን እስካሁን ነፍሳችንን አኑረውታል፣ በቂ ድጋፍ እየተደረገልን አይደለም ይላሉ፡፡ “ዋናው ጥያቄያችን ወደ ቤታችን መልሱን ነው፡፡ ነጻነታችንን እናግኝ፣ ነገር ግን እስካሁን የተሰጠን ምላሽ የለም፤ በዛው የቀሩ ወጣቶች እየታፈኑ እየተወሰዱ ነው፤ አሰቃቂ እርምጃ እየወሰዱ ነው” ብለዋል፡፡

እኒህ እናት ልጆቻቸው ከሰው ፊት ቀርበው፣ የሰው እጅ ሲያዩ አብዝተው እንደሚያዝኑ እና እንደሚያለቅሱም ነግረውናል፡፡ “ ብዙ የለመዱ ልጆች ሲያጡ ያሳዝናል፤ ሌሎች ልጆች እየበሉ የእኛ ጦማቸውን ሲያድሩ እናለቅሳለን፤ መንግሥት ለእናት እና ለሕጻናት ሲል ሀገሩን ሰላም አድርጎ ወደ ቦታችን ይመልሰን” ነው ያሉት፡፡ ችግርን የሚያውቁ እና የሚረዱ ሁሉ ያግዙን፣ አይርሱን፣ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ተባበሩን ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡

ከራያ አላማጣ ተፈናቅለው በቆቦ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ የሚገኙት ሌላኛው አባት ሕይወት በመጠለያ ውስጥ እንደከበዳቸው ነግረውናል፡፡ “ ከሞቀ ቤታችን ልጆች ወልደን፣ አሳድገን፣ ድረን ኩለን ወግ ማዕረግ፤ የልጅ ልጅም አይተናል፤ አሁን ግን የሚበላም የሚጠጣም በሌለበት መጠለያ ውስጥ እየኖርን ነው፡፡ በመጠለያ ውስጥ ረሃብ፣ ችግር አለ፤ በሽተኛ በወቅቱ አይታከምም፤ እኔ የስኳር ታማሚ ነኝ ነገር ግን በወቅቱ አልታከምም፣ በአደጋ ውስጥ ነው ያለነው” ነው ያሉት፡፡

በችግር ውስጥ ነው ያለነው፣ ሕጻናት፣ አረጋውያን እየተቸገሩ፣ እየራባቸው ነወ ብለዋል፡፡ እርዳታ እንዲደረግላቸው በተደጋጋሚ ጠይቀው እየተደገፉ አለመኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ወደ ቀያቸው ለመመለስ በተደጋጋሚ እየጠየቁ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ “ ተወልደን ባደግንበት ሀገር፣ በወራሪዎች ተፈናቅለን በመጠለያ ውስጥ እየኖርን ነው፣ እኛ ደማችንም፣ ስጋችንም አማራ ነው፣ ለኢትዮጵያውያን እና ለመንግሥት የምናስተላልፈው ድጋፍ እንዲያደርጉልን ነው” ብለዋል፡፡ ወራሪዎችን አንፈልጋቸውም፣ አንወዳቸውም፣ በግድ ነው የእኛ ናችሁ እያሉ መከራችን የሚያበዙት፣ ወጣቶች ከእነርሱ ጋር እየተጋፈጡ ነው፤ አንፈልጋቸውም፣ መንግሥትም ወራሪዎችን አስወጥቶ፣ ሰላሙን አስከብሮ እንዲመልሰን እንሻለን ነው ያሉት፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በመንግሥት እና በረጂ ድርጅቶች የሰበዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ እየተሰጠ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ መንግሥት በሐምሌ/2016 ዓ.ም 1 ሚሊዮን 183 ሺህ በላይ ወገኖችን ድጋፍ ለማድረግ ለይቷል ነው ያሉት፡፡ ረጂ ድርጅቶች ደግሞ ሰሜን ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ እና ዋግኸምራ ላይ ድጋፍ እያደረጉ መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ የራያ እና የጠለምት አካባቢዎችን ጨምሮ ከ978 ሺህ በላይ ወገኖች ይደገፋሉ ነው የተባለው፡፡ በአጠቃላይ በሐምሌ/2016 ዓ.ም ብቻ ከ2ሚሊዮን በላይ ወገኖች የሰበዓዊ ድጋፍ ይደረግላቸዋል ነው ያሉት፡፡

የድጋፍ አቅርቦቱ ጥሩ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ ዋናው ችግር በጸጥታ ችግር ምክንያት በሁሉም አካባቢዎች መግባት አለመቻሉ ነው ብለዋል፡፡ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ያልደረሱባቸው አካባቢዎች መኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ጎርፍን ጨምሮ ሌሎች አደጋዎች ሊደርሱ ይችላሉ በሚል መጠባበቂያ እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት በበጀተው 200 ሚሊዮን ብር ግዥ ተፈጽሞ ወደ ማዕከላዊ መጋዘን እየገባ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡

በክልሉ ያለው ሁኔታ ምቹ ከኾነ ማቅረብ እንደማይቸገሩም አንስተዋል፡፡ በራስ አቅም የሰበዓዊ ድጋፍ ለመሸፈን እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በሕወሓት ታጣቂዎች ለተፈናቀሉ ወገኖችም ድጋፍ እየቀረበ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ወደ ማዕከል ላልገቡ ወገኖችም ባሉበት ድጋፍ እንደሚደረግ ነው የገለጹት፡፡ ራያ አካባቢ የተፈናቀሉ ወገኖች ብዙዎች ተመልሰዋል፤ ላልተመለሱትም ተመድቧል፤ ባሉበትም ኾነው ድጋፍ ይደረግላቸዋል ነው ያሉት፡፡

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ በክልሉ የመጠለያ ችግር አለ፡፡ በሰሜን ወሎ ጃራ እና ደብረ ብርሃን በመጠለያ ውስጥ ያሉ ወገኖች የተሻለ መጠለያ እንዳላቸው የተናገሩት ኮሚሽነሩ በደቡብ ወሎ ያሉ ወገኖች ግን የመጠለያ ችግር እንዳለባቸው ነው የገለጹት፡፡ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ጥናት እየተጠና መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ወገኖች በመጠለያ ሲኖሩ ብዙ ነገሮች እንደሚጎድሉባቸው አንስተዋል፡፡ ወደ ቀደመ ቀያቸው የተመለሱ ወገኖች መኖራቸውንም አመላክተዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ድርቅ የነበረባቸው አካባቢዎች በአብዛኛዎቹ ዝናብ መጣሉን የተናገሩት ኮሚሽነሩ በቀሩት ጥቂት ቀበሌዎችም ዝናብ ይጥላል ተብሎ ይጠበቃል፤ ዝናብ በወቅቱ ከጣለ ደግሞ መደበኛ የመኸር ምርት ይቀጥላል፤ ይሄም ወገኖች ራሳቸውን እንዲችሉ ያደርጋቸዋል ነው ያሉት፡፡ ያም ኾኖ ግን ዋግኸምራ እና ሰሜን ጎንደር የመንግሥትን የተለየ ትኩረት ይሻሉ ብለዋል፡፡ ከመደበኛው ልማት የተሻገረ ዕቅድ ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት፡፡

በክልሉ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ወገኖች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፤ ከሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች ውጭ ከ2 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ወገኖች የሰበዓዊ ድጋፍ እየቀረበላቸው ነው፡፡ በእርዳታ ሰውን መለወጥ አይቻልም፣ ሕይወትን ማቆዬት ይቻላል እንጂ ያሉት ኮሚሽነሩ ወገኖችን በዘላቂነት ማቋቋም እና ራሳቸውን የሚችሉበትን መንገድ መቀየስ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

በክረምቱ ለሚደረገው ድጋፍ ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ማኅበረሰቡ በአካባቢው ላሉ ወገኖች ድጋፍ ማድረጉን መቀጠል እንደሚገባውም አንስተዋል፡፡ በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን ከችግር ለማውጣት የሁሉም ርብርብ አስፈላጊ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጎንደር ከተማን ችግር መፍታት የሚቻለው መሪዎች እና የመንግሥት ሰራተኞች ተግባብተው መሥራት ሲችሉ እንደኾነ ተጠቆመ።
Next articleበደቡብ ወሎ ዞን 329 አዲስ የመጠጥ ውኃ ተቋማት ተገንብተው ለተጠቃሚዎች ክፍት ኾኑ፡፡