”8 ነጥብ 2 ሚሊየን ተሳታፊ ያለው የክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራ ተጀምሯል” የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ

23

ባሕር ዳር: ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኅላፊ ተሾመ ፈንታው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባለፉት ዓመታት ሲከናወን የቆየ ሥራ መኾኑን ገልጸዋል።

በሂደትም የተሳትፎ ጥራት እና የኅብረተሰቡ ትኩረት መጨመሩን ተናግረዋል። በዘንድሮው ክረምትም 8 ነጥብ 2 ሚሊየን ተሳታፊ ያለው የበጎ ፈቃድ ሥራ ተጀምሯል ብለዋል። በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ 6 ቢሊየን ብር የሚገመት ሥራ እንደሚሠራ እና 13 ሚሊዮን የሚኾነውን የክልሉ ማኅበረሰብ እንደሚጠቀም ምክትል ኅላፊው ገልጸዋል።

አቶ ተሾመ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የአረንጓዴ አሻራ፣ የከተማ ጽዳት እና ውበት፣ የጤና፣ የትምህርት እና የሰላም ሥራዎችን ጨምሮ በ14 የሥራ መስኮች ላይ ያተኩራል ብለዋል። በጎ ፈቃድ አገልግሎት በኅብረተሰቡ ዘንድ ባሕል እንዲኾን ምን እየተሠራ ነው ሲል አሚኮ ላቀረበላቸው ጥያቄ በክረምት እና በበጋ የሚፈጸም የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በማቀድ ከተማሪ እና ወጣቶች በተጨማሪም ሌላው የኅብረተሰብ ክፍልም እንዲሣተፍ እየተደረገ መኾኑንን ገልጸዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማኀበረሰቡ ውስጥ ወጥነት እና አሳታፊነት እንዲኖረው በሀገር አቀፍ ደረጃ የፖሊሲ ማዕቀፎችን የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleወጣቶች ደም በመለገስ ሕይዎት ሊታደጉ እንደሚገባ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ጠየቀ።
Next articleየውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ አዲስ ለተሾሙ አምባሳደሮች የሥራ ስምሪት መመሪያ ሰጡ።