
እንጅባራ: ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የብሔረሰብ አስተዳደሩ ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ከእንጅባራ ጠቅላላ ሆስፒታል ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የደም ልገሳ መርሐ-ግብር በእንጅባራ ከተማ ተካሂዷል። በመርሐ-ግብሩ ላይ ተገኝተው ደም የለገሱ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችም ደም በመለገስ በደም እጦት የሚጠፋውን ሕይዎት መታደግ በመቻላቸው ደስታ እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።
ወቅቱ በተለያዩ ምክንያቶች ከፍተኛ ደም የሚያስፈልግበት ወቅት ነው ያሉት ደም ለጋሾቹ ኅብረተሰቡ ደም መለገስን ባህሉ ሊያደርገው ይገባል ብለዋል። የእንጅባራ ጠቅላላ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አዲሱ ሙሉሰው በክልሉ የተፈጠረውን ግጭት እና እየተባባሰ የመጣውን የወባ ወረርሽኝ ተከትሎ በሆስፒታሉ ከፍተኛ የደም እጥረት መከሰቱን ተናግረዋል።
ሆስፒታሉ በአሁኑ ወቅት በቀን ከ20 ዩኒት በላይ ደም እንደሚያስፈልገው የገለጹት ሜዲካል ዳይሬክተሩ አሁን ላይ ያለው አቅርቦት አናሳ በመኾኑ የደም ልገሳው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል። የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ቃለአብ ከሃሊ የዘንድሮው የወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሕዝቡን አንገብጋቢ ችግሮች በሚፈቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የደም እጥረት ከተለያዩ ከማኅበረሰቡ አንገብጋቢ ችግሮች መካከል አንዱ እንደኾነ ያነሱት ኀላፊው በተያዘው የክረምት ወቅት ወጣቶችን በማሥተባበር 500 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መታቀዱንም ገልጸዋል። ወጣቶች ደም በመለገስ በደም እጦት የሚሞቱ ሰዎችን ሕይዎት ሊታደጉ እንደሚገባም መምሪያ ኀላፊው አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!