“የሰላም ካውንስሉ ከየትኛው ወገን የሃሳብ ጥገኝነት ኖሮት የሚሠራ አይደለም” የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል

23

ባሕር ዳር: ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር እና በሰሜን ጎጃም ዞን የተመረጡ የሰላም ካውንስል አባላት ተወያይተዋል፡፡ በውይይቱ የአማራ ክልል የሰላም ካውስንል ሠብሣቢ ያየህይራድ በለጠን ጨምሮ ሌሎች የሰላም ካውንስል አባላት ተገኝተዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ እና የሰሜን ጎጃም ዞን የሰላም ካውንስል ሥራ አሥፈጻሚ ይደግ ማሩ የሰላም ካውንስሉ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ አባላትን እና የሥራ አሥፈጻሚዎችን እያዋቀረ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ መዋቅሩ እስከ ቀበሌ ድረስ እንደሚወርድም አንስተዋል፡፡ የሰላም ካውንስሉ ተግባር መንግሥት እና የታጠቁ ኀይሎችን በማመቻቸት ወደ ውይይት መድረክ እንዲመጡ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

እስካሁን ድረስ ባደረጓቸው ግንኙነት ጥሩ ምላሽ እያገኙ መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡ በቀጣይ የሚደርሱበትን ውጤት ለሕዝብ ይፋ እያደረጉ እንደሚሄዱም አስታውቀዋል፡፡ ሥራ አሥፈጻሚው ድርድሩን የሚወስኑት የታጠቁ ኀይሎች እና መንግሥት መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ማደራደር የሰላም ካውንስሉ ሥልጣን እና ተግባር አለመኾኑም አስታውቀዋል፡፡

የታጠቁ ኀይሎች እና የመንግሥት አካላት ሁለቱም የማኀበረሰቡ ልጆች፣ ወንድሞች እና እህቶች መኾናቸውን ያነሱት ሥራ አሥፈጻሚው ሁለቱ ኀይሎች ወደ ድርድር መንገድ መጥተው መልካም ወደ ኾነው ነገር እንዲሄዱ ማኅበረሰቡ ግፊት ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡ ካውንሰሉ ከሁለቱም ወገን ገለልተኛ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የሁለቱንም ወገኖች ሃሳብ አያራምድም፣ የካውንስሉ ዓላማ ሁለቱም ኀይሎች በመካከላቸው የፈጠሩትን መራራቅ እንዲፈቱ እና እንዲቀራረቡ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

የሰላም ካውንስሉ ከየትኛውም ወገን የሃሳብ ጥገኝነት ኖሮት የሚሠራ አይደለም ነው ያሉት፡፡ የሰላም ካውንስሉ አባላት በሙሉ የየትኛውንም አካል ደግፈው ሃሳብ እንደማይሰጡም አስገንዝበዋል፡፡ የትኛውም አካል እንዲያውቅ የምንፈልገው የሰላም ካውንስሉ ከሁለቱም ወገኖች በሚነሱ ሃሳቦች ላይ ድጋፍ የማይሰጥ እና ገለልተኛ ወገን መኾኑን ነው ብለዋል፡፡

የሰላም ካውንስሉ ሁለቱ አካላት በፈለጉት አካል እና በፈለጉት ቦታ እንዲደራደሩ የማመቻቸት ሥራውን እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡ ሕዝቡ እረፍት ሊያገኝ ይገባል ያሉት ሥራ አሥፈጻሚው በተለይም የግብርና እና የትምህርት ሥራ በየትኛውም አካል እንዳይከለከሉ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

የሰላም ካውንስሉን ኀላፊነት እና ተግባር በተመለከተ ለማኅበረሰቡ ግልጽ የማድረግ ሥራዎች በምሁራን የታገዘ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ግልጽ የኾነ ሃሳብ እንዲኖረው እንደሚፈለግም ገልጸዋል፡፡ የአማራ ክልል ሰላም ካውንስል ሠብሣቢ ያየህይራድ በለጠ የሰላም ካውንስሉ ኀላፊነት እና ተልዕኮ መንግሥት እና የታጠቁ ኀይሎች ለድርድር እና ለውይይት እንዲቀራረቡ ማመቻቸት መኾኑን ነው ያመላከቱት።

የሰላም ካውንስሉ አደራዳሪም ኾነ ተደራዳሪ አይደለም ያሉት ሠብሣቢው ሁለቱ ወገኖች በመረጡት አደራዳሪ፣ በፈለጉት ቦታ ወደ ጦርነት ያስገባቸውን ልዩነት በማቅረብ በሰለጠነ መንገድ እንዲወያዩ የሚያመቻች መኾኑን አመላክተዋል። ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ኅብረተሰቡ ከጎናችን እንዲቆም እና ሁለቱ ወገኖች ወደ ድርድር፣ ውይይት እና እርቅ እንዲመጡ እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም እና ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ልምዶችን የሚደግፍ የፋይናንስ ፍላጎትን ማስረፅ ያስፈልጋል ተባለ።
Next article“በማደግ ላይ ባለው ዲጂታል ኢኮኖሚ ከባቢ የመጪው ትውልድ ኢትዮጵያውያንን ለማብቃት ታልሞ የተጀመረ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)