
ባሕር ዳር: ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአዘዞ-ጎንደር የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ እንዲቻል ግንባታው በራስ ኀይል የጎንደር መንገድ ጥገና ዲስትሪክት እየተከናወነ ነው።
አጠቃላይ የመንገዱ ርዝመት 12 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲኾን የፕሮጀክቱን ቀሪ ሥራዎች በፍጥነት ለማጠናቀቅ እንዲቻል ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት አሁን ላይ በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የጎንደር መንገድ ጥገና ዲስትሪክት ግንባታውን ተረክቦ እየሠራ ይገኛል።
21 ሜትር የጎን ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ በመገንባት ላይ በሚገኘው በዚሁ ፕሮጀክት አሁን ላይ የአስፋልት፣ የሰብቤዝ፣ የቤዝኮርስ፣ የአቃፊ ግንብ እና የውኃ መፋሰሻ ቱቦ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። በዚህ ዓመትም በአንድ አቅጣጫ በኩል ያለውን የመንገዱን ክፍል ሙሉ በሙሉ አስፋልት ለማልበስ ዕቅድ ተቀምጧል።
መንገዱ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ የከተማውን የትራፊክ እንቅስቃሴ የሚያቃልል እንደኾነም ነው የተገለጸው፡፡ መንገዱ ወደ ሰሜን ጎንደርም ኾነ ወደ ተለያየ አቅጣጫ የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ውስጥ ለውስጥ መሄድ ሳይጠበቅባቸው በቀጥታ ለማለፍ ያስችላቸዋል ነው የተባለው። ፕሮጀክቱ የፌዴራል መንግሥት በመደበው 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ እንደሚገኝ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!