
ገንዳ ውኃ: ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በያዝነው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ124 ሺህ በላይ ወጣቶችን ለማሳተፍ እየተሠራ መኾኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪየ አስታውቋል። በዚህ ክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አረጋዊያንና አቅመ ደካሞችን ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ በመምሪያው የወጣቶች ማካተት ንቅናቄ ተሳትፎ ቡድን መሪ አቶ ኃይለኢየሱስ መኮንን ለአሚኮ ተናግረዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በ14 የሥራ መስኮች ከ124 ሺህ በላይ ወጣቶችን ለማሳተፍ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም ቡድን መሪው ጠቅሰዋል። እንደ ቡድን መሪው ገለጻ ወጣቶቹ ሃብት በማፈላለግና በጉልበታቸው የአቅመ ደካማ እና አረጋውያን ቤት በአዲስ መገንባት፣ መጠገን፣ የእርሻ ማሳቸውን በዘር መሸፈን እና አረም በማረም አገልግሎት ይሰጣሉ።
ለአቅመ ደካሞችና አረጋውያን ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ደም ልገሳ፣ አረንጓዴ አሻራ፣ የከተማ ፅዳትና ውበት፣ የማጠናከሪያ ትምህርት እና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንደሚሠጡም አቶ ኀይለኢየሱስ ገልጸዋል። ወጣቶች በሚሰጡት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ከ333 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እና ከ141 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ለማዳን ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱንም ነው ቡድን መሪው የተናገሩት።
እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴ ለአቅመ ደካሞች እና ለአረጋዊያን 63 ሺህ ብር መሰብሰቡን፣ 7 ቤቶች መገንባታቸውን፣ 30 ሄክታር መሬት መታረሱን፣ 415 ሺህ ችግኝ መተከሉን፣ 46 ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉንም ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!