
ባሕር ዳር: ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የክልሉ መንግሥት የሠላም ካውንስሉን ጥሪ ተቀብለው ከሚመጡ የታጠቁ ኀይሎች ጋር ችግሮችን በድርድር ለመፍታት ዝግጁ ነው ሲሉ የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) ገለጹ። ኀላፊው ከኢፕድ ጋር በነበራቸው ቆይታ የክልሉ መንግሥት የሠላም ካውንስሉን ጥሪ ተቀብለው ከሚመጡ የታጠቁ ኀይሎች ጋር ችግሮችን በድርድር ለመፍታት ዝግጁ እንደኾነ አረጋግጠዋል።
በክልሉ የሠላም እና ፀጥታ ችግሮችን ተከትሎ የሕግ እና የፀጥታ ማስከበር ሥራ ሲሠራ ቆይቷል ያሉት ኀላፊው የክልሉ ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቶ በርካታ አካባቢዎች ላይ ሕዝቡ የሠላም አየር እየተነፈሰ ይገኛል ብለዋል፡፡ አንጻራዊ ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግ ከሕግ ማስከበር ጎን ለጎን መሣሪያ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ኀይሎች የሰላም ጥሪ እየተላለፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የክልሉ መንግሥት በማንኛውም መንገድ ለሠላም ምን ጊዜም በሩ ክፍት መሆኑን የገለጹት ዶክተር መንገሻ ካውስሉ ባቀረበው ጥሪ መሠረት የክልሉ መንግሥት ችግሮችን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥሪውን በፍጥነት ተቀብሏል ነው ያሉት፡፡ የክልሉ መንግሥት ግጭት አውዳሚ መኾኑን በማመን ለሰላም ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መኾኑን በመግለጽ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ እና በድርድር ለመፍታት ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መኾኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የተካሄደውን የሠላም ኮንፍረንስ ተከትሎ የታጠቁ ኀይሎች ወደ ሰላማዊ መንገድ እየገቡ እንደሚገኝ ጠቅሰው ከቀበሌ ጀምሮ በተካሄደው የሠላም ኮንፍረንስ በርካታ ሠላም ወዳድ የኅብረተሰብ ክፍል መሳተፉን ገልጸዋል፡፡ የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ከሰላም ሁሉም አካላት ተጠቃሚ መኾናቸውን አንስተዋል ያሉት ኀላፊው በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጫካ ያሉት እና መንግሥት ወደ ድርድር ሊገቡ ይገባል የሚል ጥያቄ ቀርቧል ብለዋል።
ኅብረተሰቡ ከሰላም መደፍረስ ጋር ተያይዞ መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ እና ንብረታቸው እየተዘረፈ መኾኑን መግለጻቸውን ጠቅሰው የሕክምና፣ የትራንስፖርት፣ የንግድ እና ትምህርት እንቅስቃሴዎች ላይ ጫና እንደፈጠረባቸው ተሳታፊዎች መናገራቸውን ገልጸዋል። ከሰላም የሚጠቀመው መላው ማኅበረሰቡ መኾኑን በመግለጽ ለሰላም ቁርጠኛ በመኾን ለድርድር ዝግጁ የማይኾንን ኀይል እናወግዛለን የሚሉ ሃሳቦች ማንሳታቸውን አስረድተዋል።
የሰላም እጦት በርካታ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ አሳድሯል ማለታቸውን ገልጸው ለሀገር ግንባታ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ወንድም፣ እህቶች እና ልጆች የጦርነቱ ሰለባ ኾነዋል ሲሉ መናገራቸውን ገልጸዋል። የሰላም ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች መንግሥት እና የታጠቁ ኀይሎች ወደ ድርድር መምጣት እንዳለባቸው መግለጻቸውን የተናገሩት ኀላፊው የክልሉ መንግሥት ለሠላም ድርድሩ ፈቃደኛ በመኾኑ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኀይሎች ፍቃደኛ ሲኾኑ የድርድር ሃሳቡን እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል።
የክልሉ መንግሥት ማንኛውም የታጠቀ ኀይል ወደ ሰላም ከመጣ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ በመግለጽ ሀገር የሚገነቡ ታዳጊ ሕጻናት እና ወጣቶች ስለሀገር እድገት እና ተወዳዳሪነት ማሰብ እንጂ የጥይት ድምፅ እየሰሙ ማደግ የለባቸውም እና ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ ነን ብለዋል።
ኅብረተሰቡ ከምንም በላይ እድገትን እና ለውጥን እንደሚፈልግ ጠቅሰው ለሰላም እኔ ነኝ መታገል ያለብኝ በሚል የሚደርስበት ተፅዕኖ ተቋቁሞ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሕዝቡ በጫካ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ኀይል ሰላም እንዲሰፍን ወደ ሰላማዊ ድርድር መምጣት አለባቸው ማለታቸውን ገልጸው መንግሥትም የሕዝቡን ጥያቄ ተቀብሎ እጁን ዘርግቶ እየጠበቀ እንደሚገኝም ገልጸዋል። በመጨረሻም አዲሱ ትውልድ ሀገር መረከብ የሚችለው መማር እና መመራመር የሚችሉት ሰላም ሲኖር መኾኑን በመግለጽ በጫካ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ወንድሞች ሁሉም ነገር በጦርነት ሊፈታ አይችልምና አንድ ኾነን ከችግር መውጣት አለብን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!