
ባሕር ዳር: ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር እና በሰሜን ጎጃም ዞን የተመረጡ የሰላም ካውንል አባላት የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው። በውይይቱ የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ሠብሣቢ ያየህይራድ በለጠ፣ የሰሜን ጎጃም ዞን አሥተዳደሪ አሠፋ ጥላሁንን ጨምሮ የሰላም ካውስል አባላት ተገኝተዋል።
በውይይቱ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ሠብሣቢ ያየህይራድ በለጠ የሰላም ካውንስሉ በጫካ የሚገኙ ወንድሞቻችን እና መንግሥትን አሁን ካሉበት ግጭት እና ጦርነት ወጥተው ወደ ድርድር እና ንግግር እንዲመጡ የሚያቀራርብ እና የሚያመቻች መኾኑን ተናግረዋል።
የሰላም ካውንስሉ ኀላፊነት እና ተልዕኮ የመንግሥት እና የታጠቁ ኀይሎች ለድርድር እና ለውይይት እንዲቀርቡ ማመቻቸት ነው ብለዋል።
የሰላም ካውንስሉ አደራዳሪም ተደራዳሪም አይደለም ያሉት ሠብሣቢው ሁለቱ ወገኖች በመረጡት አደራዳሪ፣ በፈለጉት ቦታ ወደ ጦርነት ያስገባቸውን ልዩነት በማቅረብ በሰለጠነ መንገድ እንዲወያዩ የሚያመቻች መኾኑን አመላክተዋል። ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ኅብረተሰቡ ከጎናችን እንዲቆም እና ሁለቱ ወገኖች ወደ ድርድር፣ ውይይት እና እርቅ እንዲመጡ እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል።
ማኅበረሰቡ ታዛቢ እና ተመልካች ሳይኾን ዳር ላይ ቆሞ በዝምታ ሳያይ ባላቤት ኾኖ ታሪክ የጣለበትን ወሳኝ ኀላፊነት እንዲወጣም ጥሪ አቅርባለሁ ነው ያሉት። ሁለቱ ወገኖች የአማራ ክልልን ችግር በውይይት በመፍታት በታላቅ ክብር ትወልድ የሚዘክረው ደማቅ ታሪክ እንዲጽፉም ጥሪ አቅርበዋል። ለታጠቁ ኀይሎች ባቀረቡት ጥሪ የአማራን ሕዝብ ጥያቄ የምታስመልሱ በውይይት እና በድርድር መኾኑን በመገንዘብ እጃችሁ ላይ የገባውን ዕድል ተጠቅማችሁ ወገናችሁን ነጻ አውጡት ብለዋል።
ችግሮችን በውይይት እና በድርድር በመፍታት የአማራ ሕዝብ በክብር እና በኩራት ማማ ላይ እንዲቀመጥ አድርጉት ነው ያሉት። ለመንግሥት ባቀረቡት መልዕክትም የክልሉ መንግሥት በሰላም ካውንስሉ የቀረበለትን የድርድር እና የውይይት ጥያቄ በመቀበሉ የሚመሠገን ቢኾንም የፌዴራል መንግሥት ለድርድሩ በመግለጫ የተደገፈ ዕውቅና እንዲሰጥ በትህትና በሰላም ካውንስሉ ስም ጥያቄየን አቀርባለሁ ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!