የአፍሪካ የውኃማ አካላት ሳምንት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

14

ባሕር ዳር: ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕርና ውቅያኖስ ሀብቶች ላይ ግንዛቤ መፍጠር አላማው ያደረገ የአፍሪካ የውኃማ አካላት ሳምንት (ብሉ ኢኮኖሚ) ዛሬ በአፍሪካ ኅብረት ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ተጀምሯል። “የአፍሪካን የብሉ ኢኮኖሚ ሕዳሴ እውን ማድረግ” በሚል መሪ መልእክት የሚከበረውን የአፍሪካ የውኃማ አካላት ሳምንት ያዘጋጁት የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን፣ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) እና አጋር አካላት ናቸው።

የአፍሪካ የውኃማ አካላት ሳምንት የተመለከተ አውደ ጥናት በመካሄድ ላይ ይገኛል። በአውደ ጥናቱ ላይ የአፍሪካ ኅብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ “ብሉ ኢኮኖሚ” እና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ፣ የኖርዌይ የዓለም አቀፍ ልማት ምክትል ሚኒስትር ቦርግ ሳንድካየር፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን መሪዎች፣ የኅብረቱ አባል ሀገራት ተወካዮች፣ የዘርፉ ተዋንያንና አጋር አካላት ተሳታፊ ኾነዋል።

ሳምንቱ የባሕርና ውቅያኖስ ሀብቶች ”ብሉ ኢኮኖሚ” ፅንሰ ሀሳብ ላይ ሁሉን አቀፍ መረዳት መፍጠር እንዲሁም ያላቸውን ጠቀሜታዎችና ፈተናዎች የማስገንዘብ አላማ ያለው ነው። የተለያዩ የዘርፉ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በብሉ ኢኮኖሚ ያሉ እድሎች ላይ በመምከር የጋራ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል ትርጉም ያለው ትብብርን ማጠናከር የሚያስችል ምቹ መደላድልን ይፈጥራል ተብሏል።

ፖሊሲ አውጪዎች በብሉ ኢኮኖሚ ላይ አዳዲስ የፖሊሲ ማዕቀፎችን ማዘጋጀትና በአፍሪካ የዘርፉን ኢኮኖሚ መደገፍ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ምክክርና የልምድ ልውውጥ እንደሚያደርጉ ተገልጿል። የአፍሪካ ሴቶች እና ወጣቶች በብሉ ኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግና በነሱ የሚመሩ የኢኮኖሚ ማዕቀፎችና የፈጠራ ሀሳቦችን መንደፍ ላይ ውይይት እንደሚደረግም ተመላክቷል።

የብሉ ኢኮኖሚ አማራጮች፣ ዓለም አቀፍ የውቅያኖስ ኢኮኖሚ፣ ቱሪዝም፣ የውኃ ሀብቶች ጥበቃና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲሁም ወጣቶችን ማብቃት ውይይት የሚደረግባቸው ርእሰ ጉዳዮች እንደኾኑ ኢዜአ ከአፍሪካ ኅብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል። የአፍሪካ ውኃ አካላት ሳምንት እስከ ሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።

የአፍሪካ የባሕርና የውቅያኖስ ቀን ከነገ በስቲያ ይከበራል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ ሴቶች ወደ አመራር ሰጪነት እንዲመጡ ውጤታማ ሥራ እየሠራች መኾኑን የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና ሙሐመድ ገለጹ።
Next article“ችግሮቻችሁን በውይይት እና በድርድር ፈትታችሁ የአማራ ሕዝብ በክብር እና በኩራት ማማ ላይ እንዲቀመጥ አድርጉት” የሰላም ካውንስል ሠብሣቢ ያየህይራድ በለጠ