
ሁመራ: ሐምሌ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ “በጎነት ከሀሳብ ይጀምራል” በሚል መሪ መልእክት የክረምት በጎ አድራጎት ማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ በሁመራ ከተማ አካሂዷል።
በ13 የሥራ ዘርፎች ከ32 ሺህ በላይ ወጣቶችን በክረምት በጎ አድራጎት ተሳታፊ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ በውይይቱ ተጠቁሟል። የበጎ አድራጎት ተግባሩ በደም ልገሳ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፣ ችግኝ በመትከል፣ ለተማሪዎች የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት እና በሌሎች ተግባራት እንደሚከናወን ተገልጿል።
ዞኑ ያለ በጀት የሚንቀሳቀስ በመኾኑ በርካታ ተማሪዎች በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን እንዳቋረጡ ያነሱት የውይይቱ ተሳታፊዎች በክረምት በጎ አድራጎት ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት በቀጣይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዳይርቁ መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
በ2015 በጀት ዓመት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ20 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ ከ70 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም ተገልጿል። የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ብርሃን ነጋ የወጣቶች ተሳትፎ ከ1 ሚሊዮን ብር የሚገመት እንደነበርም ገልጸዋል።
በ2016 በጀት ዓመት በክረምት የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ ከ279 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራ ያነሱት ወይዘሮ ብርሃን የወጣቶች ተሳትፎ ወደ ገንዘብ ሲቀየር ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚኾን ተናግረዋል። ወጣቱ ትውልድ የበጎ አድራጎት ተግባራትን በክረምት ብቻ ሳይኾን ዓመቱን ሙሉ ሊያከናውነው የሚገባ መኾኑን ኀላፊዋ አሳስበዋል።
ዘጋቢ :- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!