“የአካባቢን ውበት ለመጠበቅ እና መልካም ሥነ ምህዳር ለመፍጠር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አይተኬ ሚና አለው” ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ

12

ደብረ ማርቆስ: ሐምሌ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “የምትተክል ሀገር ፣ የሚያጸና ትውልድ”በሚል መሪ መልዕክት በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የአረንጓዴ አሻራ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ የአካባቢን ውበት ለመጠበቅ እና መልካም ሥነ ምህዳር ለመፍጠር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አይተኬ ሚና አለው ብለዋል። በመኾኑም ኅብረተሰቡ ጥላቻን እና ልዩነትን ወደጎን በመተው ሰላምን እና አንድነትን በማጽናት ለዜጎች ምቹ ሀገርን ማስረከብ ይጠበቅበታል ነው ያሉት።

ችግኝ መትከል ብቻ ሳይኾን የተከልናቸውን ችግኞች በመንከባከብ ማጽደቅ ይገባልም ብለዋል ከንቲባው። የደብረ ማርቆስ ከተማ ግብርና መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ሃብታሙ ሽመልስ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ በአንድ ጀምበር ከ9 ሺህ 500 በላይ ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዟል ብለዋል፡፡

በተያዘው የክረምት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርም ከ8 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ የደን፣ የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል እንደታቀደም ተናግረዋል። በተያዘው ክረምት በደን፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞች 374 ነጥብ 8 ሄክታር መሬት ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም ነው ተወካይ ኀላፊው ያስረዱት።

በከተማ አሥተዳደሩ በባለፈው ዓመት የተተከሉ ችግኞች 82 በመቶዎቹ ፀድቀዋል ያሉት ተወካይ ኀላፊው በዚህ ዓመት የተተከሉ ችግኞች ሙሉ በሙሉ እንዲፀድቁ አካባቢውን ከእንሰሳት ንክኪ ነፃ የማድረግ ሥራ እና እንክብካቤ የሚያደርጉ ሠራተኞች መቀጠራቸውንም ተናግረዋል። በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ችግኝ ሲተክሉ አሚኮ ያገኛቸው የከተማዋ ነዋሪዎችም የተከሏቸውን ችግኞች ተንከባክበው በማሳደግ ንፁህ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ የኾነች ከተማን ለመፍጠር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል።

በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ የማስጀመሪያ መርሐ ግብርም የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መንበሩ ዘውዴን ጨምሮ የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች እና ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡- አማረ ሊቁ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር ተወያዩ።
Next articleበክረምት በጎ አድራጎት መርሐ ግብር ከ32 ሺህ በላይ ወጣቶችን ለማሳተፍ እየተሠራ መኾኑን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስታወቀ።