የታዳጊ ሀገራት የልማት ጥያቄ ሊደመጥ እና ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀሥላሴ ጠየቁ።

45

አዲስ አበባ: ሐምሌ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)አራተኛው ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለዘላቂ ልማት ጉባኤ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ ነው። ጉባኤው ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት እና ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ፋይዳው የጎላ እንደኾነ ተገልጿል።

የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት የተመጣጠነ እንዲኾን ታዳጊ ሀገራት የሚያነሷቸው ጥያቄዎች መደመጥ እና ምላሽ ማግኘት እንዳለባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀሥላሴ በመድረኩ አንስተዋል። በታዳጊ ሀገራት ያለው ስር የሰደደ ድህነት እና ስደት እንዲቀንስም የዕዳ ቅነሳ መደረግ እንዳለበት በአበክሮ ከተነሱ ነጥቦች ይጠቀሳሉ።

በታዳጊ ሀገራት ላሉ ዜጎች የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን ማሻሻል እና አካታችነትን ማስፈን፤ ሕገወጥ የፋይናንስ ፍሰትን መከላከል እና ፍትሐዊነቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ተብሏል። ለታዳጊ ሀገራት አስፈላጊው የዕዳ ቅነሳ እንዲደረግላቸው እና ኢ-ፍትሐዊ የገንዘብ ፍሰትም መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ ያነሱት ደግሞ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ናቸው።

የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ አጋርነትን በማጎልበት የልማት ፕሮጀክቶችን በገንዘብ መደገፍ እና የኢኮኖሚ ዕድገትን በማጎልበት ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት እንደሚያስፈልግም ነው የገለጹት። ጉባኤው ለዘላቂ ልማት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ዘዴዎችን ለማጎልበት በባለድርሻ አካላት መካከል ውይይት እና ትብብርን ለማመቻቸት ፋይዳው የጎላ እንደኾነም ነው ያብራሩት።

ጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄዱ የኢትዮጵያን አቅም ማደግ ከማሳየቱም በላይ ለምትጠይቃቸው የልማት ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለማግኘትም አስተዋጽኦው የጎላ ነው ተብሏል።

ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሠራዊቱ ከሚሰጠው ሀገራዊ ግዳጅ ባሻገር ኅብረተሰቡን የሚያግዙ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙ ብርጋዴል ጄኔራል ወርቅነህ ጉደታ ገለጹ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር ተወያዩ።