ሠራዊቱ ከሚሰጠው ሀገራዊ ግዳጅ ባሻገር ኅብረተሰቡን የሚያግዙ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙ ብርጋዴል ጄኔራል ወርቅነህ ጉደታ ገለጹ።

35

ሁመራ: ሐምሌ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በቃብትያ ሁመራ በብዓከር ቀበሌ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ተካሂዷል። በመርሐ ግብሩ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የስሜን ምዕራብ ዕዝ የ503ኛ ኮር አባላት እና የብዓከር ከተማ ነዋሪዎች ተሳታፊ ኾነዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት የሀገርን ሰላም ከማስጠበቅ ባሻገር ከከተማ ነዋሪዎች ጋር በመቀናጀት ለሀገር ኢኮኖሚ ጠቀሜታ የሚሰጡ ችግኞች መትከላቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የ503ኛ ኮር ዋና አዛዥ ብርጋዴል ጀኔራል ወርቅነህ ጉደታ የሠራዊቱ አባላት የሀገርን ሰላም እና ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ባሻገር በተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ በመሠማራት ኅብረተሰቡን በማገዝ ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል። በከተማዋ ከ100 በላይ ለሚኾኑ እና በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ለኾኑ ተማሪዎች የዩኒፎርም፣ የደብተር እና የእስክርቢቶ ድጋፍ መደረጉን አንስተዋል፡፡ ቤታቸው የፈረሰባቸውን አቅመ ደካሞች ቤት በመሥራትም ሠራዊቱ በጎ ተግባር መሥራት እንደቻለም ተናግረዋል።

በቀጣይም የሠራዊቱ አባላት በበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ እያደረጉት ያለውን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል። የሠራዊት አባላቱ ከሚሰጣቸው ሀገራዊ ግዳጅ ባሻገር በችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በመገኘት ለሀገር ኢኮኖሚ ጠቀሜታ የሚሰጡ ችግኞችን መትከላቸውን ገልጸዋል።

በወረዳው በ2016 በጀት ዓመት ከ151 ሺህ በላይ ችግኞችን በ8 ቀበሌዎች ለመትከል እየተሠራ እንደሚገኝ የቃብትያ ሁመራ ወረዳ ግብረና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሳሙኤል ሰለሞን ገልጸዋል። ለምግብ አገልግሎት የሚውሉ የአትክልት እና ፍራፍሬ ተክሎችን እና ለአፈር እና ውኃ ጥበቃ የሚያገለግሉ አትክልቶችን በስፋት ለመትከል እየተሠራ እንደሚገኝም አንስተዋል።

ችግኝ በመትከል ላይ ያገኘናቸው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት የሚሰጣቸውን ግዳጅ ከመፈጸም ባለፈ ለሀገር ኢኮኖሚ ጠቀሜታ የሚሰጡ ችግኞችን እየተከሉ እንደሚገኙ ነግረውናል። የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁም እንክብካቤ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል። የበዓከር ቀበሌ ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደጀን በመኾን ከአባላቱ ጋር በመተባበር በርካታ ችግኝ መትከላቸውን አንስተዋል። በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ 30 ሺህ ችግኞች ተተክለዋል።

ዘጋቢ :- ያየህ ፈንቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የልማት ሥራዎችን ማከናወኑን የባሶና ወራና ወረዳ አማራ ልማት ማኀበር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
Next articleየታዳጊ ሀገራት የልማት ጥያቄ ሊደመጥ እና ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀሥላሴ ጠየቁ።