በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ የሚሠሩ ጥናቶች የምክክርን ስኬታማነት ለመመዘን ያስቀመጧቸው የመነሻ መስፈርቶች ምን ይኾኑ?

13

ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት በተለያዩ መንገዶች ይታያል፡፡ የሥነ ምክክር መዛግብት እንደሚያሳዩት የተለያዩ ሀገራት ምክክርን ለማድረግ ሲወጥኑ በሂደቱ ፍፃሜ ላይ የሚጠብቋቸው ውጤቶች መኖራቸው ግድ ይላል፡፡
በዚህም መሠረት ሀገራዊ ምክክሩ የታሰበለትን ዓላማ ማሳካቱ ለውጤታማነቱ ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡

በዘርፉ የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ሀገራት የምክክር ሂደቱን የጀመሩበት ምክንያት እንደመለያየቱ መጠን የምክክር ውጤቶቻቸውም በዛው ልክ ሲለያይ ይስተዋላል፡፡ ከዚህም አኳያ የምክክር ሂደቶቹ ስኬታማነት እንደየዓውዱ የራሱን ቀለም ይዞ ይመጣል፡፡ ይህ ሲባል ግን የምክክር ሂደቶችን ስኬታማነት ወጥነት ባለው መንገድ መመዘን እንደማይቻል ተደርጎ መታሰብ የለበትም፡፡

በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ የሚሠሩ ጥናቶች የምክክርን ስኬታማነት ለመመዘን የመነሻ መስፈርቶችን አስቀምጠዋል፡-
👉 የምክክሩ ውጤት በተለያዩ አካላት መካካል የነበሩ ስጋቶችን እና ቅራኔዎችን ለመፍታት ግልጽ የመፍትሔ ሃሳቦችን ማምጣት ሲችል
👉በምክክር ሂደቱ ተሳታፊ የነበሩ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች እና ባለድርሻ አካላት በሂደቱ ለሚገኙ ውጤቶች ተገዥ ሲኾኑ እና የመፍትሔ ሃሳቦቹም ላይ ስምምነት ሲኖራቸው
👉በሀገራዊ ምክክሩ ውጤቶች ላይ የትኛውም አካል እጁን ሳያስገባ እና ግጭቶች ሳይፈጠሩ ብሎም ውጤቶቹ በታቀደው መሠረት ለትግበራ ሲቀርቡ
👉ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተጨባጭ የኾኑ የሰላም መንገዶችን ለመተግበር ስምምነቶች ላይ ሲደርሱ
👉የሀገራዊ ምክክር ውጤቶችን ወደ መሬት አውርዶ ለመተግበር የሚያስችል ግልጽ ፍኖተ ካርታ ተቀርጾ ለአፈፃፀም ሂደቱ የሚመጥን የክትትል እና ምዘና ሥራዎች ሢሠሩ የሚሉት እንደሚገኙበት ይገልጻሉ፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መቋረጥ
Next articleቋሚ ኮሚቴው የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮን የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም እየተገመገመ ነው፡፡