የሕዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ ለአማራ ልማት ማኅበር ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ተመላከተ፡፡

20

ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ማኅበረሰብን በማሳተፍ በትምህርት፣ በጤና እና በሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራዎችን የሚሠራ ተቋም ነው፡፡ በሠራቸው ሥራዎችም በክልሉ በርካታ ለውጦችን አሳይቷል፡፡ የአልማ የአባላት ልማት እና በጎፈቃድ አገልግሎት ዳይሬክተር ጌቴ ሙላት ከአልማ ዋና ዋና ግቦች መካከል አንደኛው ሕዝባዊ መሠረትን ማስፋት መኾኑን ገልጸዋል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ማስፋፋት እና አባላትን ማፍራት ላይ በትኩረት እንደሚሠራም አንስተዋል፡፡ አልማ ከ98 ሺህ በላይ የሚኾኑ በጎ ፈቃደኞች እንዳሉትም አመላክተዋል፡፡ አልማ ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚልቁ አባላት እንዳሉት ያነሱት ዳይሬክተሩ የሚሠበሠበው ሃብት በአካባቢው ለፕሮጀክት ትግበራ እንደሚውል አንስተዋል፡፡ አልማ ለሕዝብ የሚሠራ የሕዝብ ማኅበር ነው፣ ሥራዎችን የሚሠራው በበጎ ፈቃደኞቹ እና በአባላቱ አማካኝነት ነው ብለዋል፡፡

አልማ እየሠራ ያለው ትውልድ ላይ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ትውልድ ላይ መሥራት ግድ ይለናል፤ ትውልድ ለመሥራት ደግሞ የሁሉም ድጋፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ አልማ ከኅብረተሰብ ጋር ችግርን የሚጋራ፣ ኅብረተሰብ በተቸገረ ጊዜ የሚደርስ ተቋም መኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡ ኅብረተሰቡ አልማን እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአልማ የፋይናንስ እና ሎጂስቲክስ ዳይሬክተር ቸኮል ስጦታው አልማ ባለፉት ዓመታት በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ሥራዎችን ለማከናወን በክልሉ እና ከክልሉ ውጭ ከሚገኙ አባላት መዋጮ፣ ከአጋር ድርጅቶች እና ራሱን ችሎ ባደራጃቸው የቢዝነስ ተቋማት ሃብት እንደሚያገኝ ተናግረዋል፡፡

የሚገኘውን ሃብት ለክልሉ ልማት እንደሚያውለውም አመላክተዋል፡፡ የሚገኘው ሃብት 80 በመቶው ሃብቱ በሠበሠበበት ቦታ ለልማት ሲውል፣ 2 በመቶው በክልሉ አደጋ ሲያጋጥም ምላሽ መስጪያ ይውላል ነው የተባለው፡፡ አልማ ሃብቱን በግልጸኝነት በማሥተዳደሩ ምክንያት በማኅበረሰቡ ዘንድ ታማኝ እንዲኾን እንዳደረገውም ተናግረዋል፡፡

ወደ ማኅበሩ የሚገባው ገንዘብ በግልፀኝነት እና በታማኝነት ለክልሉ ልማት እንደሚያውልም አመላክተዋል፡፡ አልማ የሚሠበሥበውን ገቢ በሠበሠበበት አካባቢ ለልማት ስለሚያውለው ማኅበረሰቡ የራሴ ብሎ እንደሚይዘውም ገልጸዋል፡፡ በሃብቱ የሚወስነው ማኅበረሰቡ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

የአልማ የፕሮጀክት ትግበራ እና ክትልል ዳይሬክተር አበረ መኩሪያ የአማራ ልማት ማኅበር ማኅበረሰብ አቀፍ የፕሮጀክት አመራር ሥልት እና ፕሮጀክት ተኮር የሕዝብ ንቅናቄን በመጠቀም ፕሮጀክቶችን እንደሚፈጽም አስታውቀዋል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍ የፕሮጀክት አመራር ሥልት ሕዝቡ በፕሮጀክት መረጣ፣ ትግበራ እና ዘላቂነት ላይ የሚሳተፍበት ነው፡፡

በሚፈልገው ፕሮጀክት አምኖበት፣ ራሱ ተሳትፎበት፣ በዓይነት፣ በጉልበት፣ በገንዘብ እያዋጣ ያቀደውን ፕሮጀክት ሠርቶ ለራሱ ጥቅም የሚያውልበት መንገድ ነው፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክት አመራር ስልት አዋጭ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የማኅበረሰብ አቅፍ አሠራር ፕሮጀክቶች በወቅቱ እንዲሠሩ እንደሚያደርግም አመላክተዋል፡፡ አልማ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን እና የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ ምላሽ ፕሮጀክቶችንም ይሠራል፡፡

አልማ ሕዝብን በማሳተፍ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡ የሕዝብ ድጋፍ እንዳለውም አንስተዋል፡፡ የሚሠሩ ፕሮጀክቶችም የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል፡፡ አልማ ስኬታማ የኾኑ የትምህርት፣ የጤና እና የሥራ ዕድል ፈጠራዎችን እየፈፀመ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ዘመን ተሻጋሪ የኾነ፣ ወቅቱ የሚመጥነውን መንገድ እየተጠቀመ ፕሮጀክቶችን እየፈጸመ የሚያስረክብ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

በጎ ፈቃደኞችም በስፋት የሚደግፉት ተቋም እንደኾነም ተናግረዋል፡፡ አልማ በርካታ ፕሮጀክቶችን እየተገበረ እንደሚገኝ የተናገሩት ዳይሬክተሩ የሕዝብ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡ አልማ ሰው ላይ የሚሠራ ተቋም መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የአልማ ቢዝነስ ልማት አሥተዳደር ዘርፍ ዳይሬክተር እና ተወካይ ምክትል ሥራ አሥፈጻሚ ዮሐንስ ታረቀኝ አልማ በዋናነት የበጎ አድራጎት ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ ማኅበሩ በዘላቂነት ለልማት የሚኾን ፋይናንስ ማግኘት በሚችልበት ሁኔታ ላይ እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

አልማ በተለይም ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ስትራቴጂካዊ ዕቅዱን አዘጋጅቶ በቢዝነስ ሥራዎች ላይ እየተሳተፈ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ ነባር ተቋማትን ማሳደግ፣ ማስፋት እና አዳዲስ የቢዝነስ ተቋማትን የማቋቋም ሥራ ነው ብለዋል፡፡ አልማ እየሠራቸው ያላቸው ሥራዎች ለክልሉ ተጨማሪ ሃብት እንደሚኾኑም ተናግረዋል፡፡

ለአብነት ዋንዛዬ ፍል ውኃ ላይ እየተሠራ ያለው ሥራ ለክልሉ ተጨማሪ ምጣኔ ሃብት እና የቱሪዝም መዳረሻ በመኾን እንደሚያገለግል ነው የተናገሩት፡፡ አትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ሥራ ላይም እየሠራ መኾኑን አመላክተዋል፡፡ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸውን ሕንጻዎች በክልሉ በሚገኙ ከተሞች እየገነቡ መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡ የኮንስትራክሽን ተቋም እንዳላቸውም ነው የገለጹት፡፡ የዓባይ የወረቀት ፋብሪካም የማኅበሩን አቅም በማሳደግ እና የክልሉን ልማት በመደገፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ በሕትመት ዘርፍ ተፈላጊ የኾኑ ሥራዎች እየተሠሩበት መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ በውጭ ሀገር ይታተሙ የነበሩ የሕትመት ሥራዎችን በራስ አቅም በማተም አስተዋጽኦ እያደረገ መኾኑን ነው ያነሱት፡፡ በቢዝነስ ልማት ላይ የሚሠሩ ሥራዎች የተቋሙን አቅም በማሳደግ፣ የክልሉን ልማት በመደገፍ የሕዝብን ተጠቃሚነት ያሳድጋል ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተተከሉ ችግኞች ፀድቀው ለሀገር ልማት የሚጠቅሙ ለማድረግ ክትትል እንደሚደረግ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ ገለጹ፡፡
Next articleየኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መቋረጥ