ያለፈው ዓመት የግብዓት አቅርቦት ክፍተት ተፈትቶ ይኾን?

31

ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት የክረምት ወራት ቀዳሚው ጥያቄ የግብዓት አቅርቦት ይቀረብልን ነበር። አርሶ አደሮች በሬ እና ቀንበሩን ፈትተው ጅራፍ አንጠልጥለው ወደ ከተማ እየመጡ አቤቱታ ያሰሙ ነበር። መሬቱ ያለ ግብዓት ፍሬ እየሰጠ አይደለም ያሉት አርሶ አደሮች ጅራፍ እያጮሁ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ችግራቸውን አሰምተው ነበር።

መንግሥት ያቀረበው የግብዓት አቅርቦት በሚፈለገው ልክ አልነበረም። በሚፈለገው ልክ ብቻ ሳይኾን በሚፈለገው ጊዜም አልደረሰም በሚል ቀሬታው ሰፊ ነበር። ከዓመት በኋላ በተመሳሳይ ወቅት ያ የአርሶ አደሮች ጥያቄ ተመልሷል። ዘንድሮ በሬ እና ቀንበር አለያይተው ጅራፍ እየያዙ ወደከተማ የሚመጡ አርሶ አደሮች የሉም። በሰኔ እና በሐምሌ ጀምበር ወደ ማሳ ይወርዳሉ እንጂ የግብዓት ያለሽ እያሉ የሚጠይቁም የሉም።

ነዋሪነታቸው በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ነው። ባለፈው ዓመት በግብዓት አቅርቦት ከተፈተኑ አርሶ አደሮች መካከል ናቸው። ገጥሟቸው በነበረው ችግር ምክንያት ሰሚ የለንም ማለት ነው? እስከ ማለት ደርሰው ነበር። ዘንድሮ ግን ያ ጥያቄ፣ ያ ችግርም ተቀርፏል ነው የሚሉት። ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ባለፈው ዓመት የግብዓት አቅርቦት አቤቱታ ከፍተኛ እንደነበር አንስተዋል። አርሶ አደሮች ችግር ላይ እንደነበሩም ገልጸዋል። በብዙ ችግር ውስጥ ነው የከረምነው፣ አንድ ኩንታል ማዳበሪያ ለሦስት ለአራት ተካፍለን ተጠቅመን ነበር ነው ያሉት።

ባለፈው ዓመት መንግሥትን በእጅጉ ያማርሩ እንደነበርም ነግረውናል። የመጣው ማዳበሪያም በአግባቡ አለመሰራጨቱን ነው የሚያስታውሱት። ያለፈው ዓመት ችግር ግን ዘንድሮ ተቀርፏል፣ ጥያቄያችን ተሰምቷል፣ የፈለግነውን አምጥቷል፣ ማግኘት የሚገባንን ነገር አግኝነተናል ነው ያሉት። ዘንድሮ ማዳበሪያ አስቀድመን ስለያዝን አናማርርም፣ ባለፈው ዓመት ከመንግሥት መጋዘን ማዳበሪያ በማጣታችን ከነጋዴ እስከ 10 ሺህ ብር ድረስ ገዝተን ነበር፣ የሚበላ ከሚታጣ በሚል ገዝተን ነበር ይላሉ። ዘንድሮ ቀድሞ መጥቷል፣ ዋጋውም ቅናሽ ነው ብለዋል።

በማዳበሪያ በኩል የተጠየቀው ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ እናመሠግናለን ነው ያሉት። ከነጋዴ በከፍተኛ ዋጋ እየገዙ የተበዘበዙ አርሶ አደሮች ዘንድሮ ከብዝበዛ መዳናቸውንም ተናግረዋል። የበቆሎ ምርጥ ዘር አቅርቦት ግን በቂ አለመኾኑን አንስተዋል። አርሳቸው እንደሚሉት የዘንድሮው ትልቁ ችግር የሰላም ችግር ነው ። መንግሥት ማዳበሪያ እስከ ቀበሌ ድረስ በማምጣት ማከፋፈሉንም አንስተዋል። በአካባቢያቸው ማዳበሪያ እንዳይወስዱ ለማድረግ የሞከሩ ታጣቂዎችን ሕዝቡ ተውን አርሰን እንብላበት ብሎ ማዳበሪያ መውሰዱንም ገልጸዋል። በወራት የደረሰውን ግብዓት በመጠቀም በስፋት እያመረቱ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ቡቃያው የሚያሳሳ መኾኑንም ነግረውናል።

ነዋሪነታቸው በሰሜን ሸዋ ዞን የኾነው ሌላኛው አርሶ አደርም የግብዓት አቅርቦት ከባለፈው ዓመት በእጅጉ የተሻለ ነው ብለዋል። ባለፈው ዓመት በእጅጉ ችግር እንደነበር አንስተዋል። የባለፈው ዓመት ዝም ብሎ ከሚቀር ተብሎ ጥቂት ነው የተወሰደው ነው ያሉት። ዘንድሮ መዝሪያ የሚኾን ግብዓት ቀድሞ እንደደረሳቸው ነው የተናገሩት። ባለፈው ዓመት አንድ ኩንታል ማዳበሪያ እስከ 13 ሺህ ብር ተሽጦ እንደነበርም አስታውሰዋል። ዘንድሮ ዋጋው የተሻለ መኾኑንም ገልጸዋል።

ነገር ግን ዘንድሮም ከፍላጎት አንጻር በቂ ማዳበሪያ አለመቅረቡንም ገልጸዋል። በአካባቢው ከፍተኛ የግብዓት ፍላጎት መኖሩንም አንስተዋል። የጸጥታ ችግሩ ፈተና መኾኑንም ተናግረዋል። ተጨማሪ ማዳበርያ እንዲቀርብ እየጠየቁ መኾናቸውን እና እንደሚመጣላቸው ምላሽ እንደተሰጣቸውም ገልጸዋል። የዘንድሮው የግብዓት አቅርቦት ከባላፈው ዓመት ጋር ለንጽጽር እንደማይቀርብም ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት ምንም አልነበረም፣ ዘንድሮ ግን ቀድሞ የደረሰውን ይዘን ተጫማሪ ስጡን ነው እያልን ያለነው ይላሉ።

የማዳበሪያ ችግር እንደሌለ በተደጋጋሚ ሲነገር መስማታቸውን የተናገሩት አርሶ አደሩ ወቅቱ ሳያልፍ እንዲደርስላቸውም ጠይቀዋል። ያለ ወቅቱ የመጣ ማዳበሪያ ካልመጣ እንደሚቆጠርም አንስተዋል። የጸጥታው ሁኔታ ችግር እንደኾነባቸውም ገልጸዋል። ሰው ለመሥራት እና በሰላም ወጥቶ ለመግባት ሰላም ያስፈልገዋል ነው ያሉት። ከስጋት ነጻ ኾነን እንድንሠራ እንፈልጋለን፣ ሰላም ከሌለ መዝራት እና ማምረት አይቻልም፣ ሰላም ይሁን ግብዓትም ይመጣል፣ ምርትም ይመረታል ይላሉ።

ከሰሞኑ ለአማራ ክልል ምክር ቤት የግብርና አካባቢ ጥበቃ እና የውኃ ሃብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም ያቀረቡት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የግብዓት አቅርቦት እና ሥርጭት በዓመቱ በትኩረት የተሠራበት ሥራ መኾኑን ገልጸዋል።

በዓመቱ በማዳበሪያ አቅርቦት እና ሥርጭት አርሶ አደሮችን ማርካት ብቻ ሳይኾን አዲስ ክብረ ወሰን ለማስመዝገብ ነው የምንሠራው ነው ያሉት። ያለፈውን ዓመት ችግር ለመፍታት ብቻ አይደለም የምንሠራው፤ አዲስ የተሻለ ውጤት በክልሉ እንዲገኝ ነው ብለዋል። ተጨማሪ የግብዓት አቅርቦት ለሚፈልጉ አርሶ አደሮች ለማቅረብ እንሠራለንም ብለዋል። የአፈር ማዳበሪያ ላይ ሕገወጥ ሥራ በሚሠሩ አካላት ላይም ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መኾኑን ነው ያነሱት። ሕገ ወጥ ተግባር በፈጸሙ አካላት ላይም እርምጃ መወሰዱን ነው ያስታወቁት።

የምርጥ ዘር አቅርቦትም በስፋት እያቀረቡ መኾኑን ነው የገለጹት። በምርጥ ዘር ሰፊ ሥራ እየተሠራ እንደኾነም ተናግረዋል። ከአፈር ማዳበሪያ እና ከምርጥ ዘር ባለፈ አርሶ አደሮች ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ እየሠሩ መኾናቸውን ነው የገለጹት። የግብርና አካባቢ ጥበቃ እና የውኃ ሃብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሜቴ አባላትም በክልሉ አንገብጋቢ ጥያቄ እና ችግር የነበረው የግብዓት አቅርቦት በጥሩ ሁኔታ እየተመለሰ መኾኑን ነው የተናገሩት። የአርሶ አደሮችን ጥያቄ በመስማት በግብዓት አቅርቦት የተሠራው ሥራ የሚደነቅ መኾኑንም አንስተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየነፋስ መውጫ ከተማ አስተዳደር በ90 ቀን እቅድ ያስገነባቸውን የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች አስመረቀ።
Next articleየተተከሉ ችግኞች ፀድቀው ለሀገር ልማት የሚጠቅሙ ለማድረግ ክትትል እንደሚደረግ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ ገለጹ፡፡