ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ ጥቅል ካፒታል ያስመዘገቡ 16 አነስተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ መካከለኛ ደረጃ ተሸጋገሩ።

32

ባሕር ዳር: ሐምሌ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ አሥተዳደሩ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ “የአምራች ኢንዱስትሪዎች ዕድገት ለሀገራችን የኢኮኖሚ ሽግግር ወሳኝ ነው” በሚል መሪ መልዕክት በሥራቸው ልቀው የወጡ አነስተኛ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ መካከለኛ ደረጃ የተሸጋገሩበትን የዕውቅና ሥነ ሥርዓት ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ አካሄዷል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እንዳሉት እንደሀገር ምጣኔ ሃብቱ ዘላቂ የሚኾነው የመሪነት ድርሻውን ኢንዱስትሪው ሲረከብ ነው ብለዋል። ከተማ አሥተዳደሩም ይህን ታሳቢ በማድግ ለ657 አምራች ኢንዱስትሪዎች የመሥሪያ ቦታ ቢሰጥም ወደ ሥራ የገቡት ግን ከ200 ያልበለጡ ናቸው ብለዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በተቀበሉት መሬት ተገቢውን ሥራ እየሠሩ ያሉትን አምራች ኢንዱስትሪዎች ይበልጥ ማትጊያዎችን በመስጠት እንደሚያበረታቱ ተናግረዋል። በአንጻሩ የተረከቡትን መሬት በማጠር ወደ ሥራ ላልገቡት አልሚዎች ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መኾኑን ጠቁመዋል።

“የተረከቡትን መሬት እንዲሠሩበት በተደጋጋሚ ዕድል እና ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ወደ ሥራ ያልገቡ “ከ40 በላይ የሚኾኑ አልሚዎች መሬት ተነጥቆ ለሌሎች ምሥጉን አልሚዎች እንዲተላለፍ በቦርድ ተወሰኗል” ነው ያሉት።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ዛሬ ከአነስተኛ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ መካከለኛ ደረጃ የተሸጋገሩትን አልሚዎች ከተማ አሥተዳደሩ በቅርብ ኾኖ ይደግፋቸዋል፤ ያግዛቸዋል፤ ያነቃቃቸዋል ነው ያሉት።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ለሴቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር የዜግነት ኀላፊነታቸውን እየተወጡ የሚገኙ አልሚ ባለሃብቶችን አመስግነዋል። ልሎች አልሚዎች የእነዚህ ምሥጉን አልሚዎች አርዓያ እንዲከተሉም ተቀዳሚ ከንቲባው አሳስበዋል።

የባሕር ዳር ከተማ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ብርሃን ንጉሴ እንዳሉት ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ ጥቅል ካፒታል ያስመዘገቡ እና ለ901 ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ 16 አነስተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ መካከለኛ ደረጃ ተሸጋግረዋል ብለዋል።

የደረጃ ሽግግር ከተደረገላቸው አንዱ የኤፍሬም እና ዮሐንስ የኀብረት ሽርክና ማኀበር ሥራ አሥኪያጅ ኤፍሬም ውቤ እንዳሉት ከታች ደረጃ ተነስተው ከፍ በማለታቸው ተደስተዋል። ከዚህ የበለጠ ለመሥራትም ሽልማቱ እንዳበረታታቸው ጠቁመዋል።

አቶ ኤፍሬም ማኀበራቸው ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል እንዳስመዘገበ ተናግረው ለ50 ሰዎችም የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። አብዛኞቹ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወገኖች ከሌላ አካባቢ የተፈናቀሉ እናቶች መኾናቸውን ተናግረዋል።

ሌላው የጁኔየር ጋርመንት ሥራ አሥኪያጅ ሙሉጌታ ውለታው እንዳሉት ከጥጥ የሀገር ባሕል ልብስ በመሸመን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ሀገር ገበያ ያቀርባሉ። ድርጅታቸው ለ300 ሰዎችም የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰላምን መሻት ብቻ ሳይኾን ሰላምን ለማስፈንም አበክረን እንሠራለን” የምዕራብ ጎንደር ዞን ነዋሪዎች
Next articleየነፋስ መውጫ ከተማ አስተዳደር በ90 ቀን እቅድ ያስገነባቸውን የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች አስመረቀ።