“ሰላምን መሻት ብቻ ሳይኾን ሰላምን ለማስፈንም አበክረን እንሠራለን” የምዕራብ ጎንደር ዞን ነዋሪዎች

33

ገንዳ ውኃ: ሐምሌ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳደር በወቅታዊ የሰላም እና ጸጥታ ጉዳይ በዞኑ ከተወጣጡ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አካሂዷል። በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ሰው አግተው በሚሊዮን የሚቆጠር ብር የሚጠይቁ ሕገ ወጦችን በማኅበረሰቡ ጥቆማ ለሕግ እንዲቀርቡ ቢደረግም በወንጀለኞች ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ በኩል መንግሥት ክፍተቶች እንዳሉበት የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

በመኾኑም መንግሥት በዞኑ እየተፈጸመ ያለውን የእገታ፣ ዘረፋ እና ግድያ ወንጀል ከማስቆም ባሻገር በወንጀለኞች ላይ የተጠናከረ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቀዋል። የተከበረ ማንነት፣ ታሪክ እና እሴት ያለው የአማራ ሕዝብ ዛሬ ላይ ግጭት ውስጥ መግባቱ አሳዛኝ መኾኑን የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

በክልሉ እየተፈጸመ ያለውን ረብየለሽ ግጭት ያወገዙት ተሳታፊዎቹ “ሰላምን መሻት ብቻ ሳይኾን በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን አስፈላጊውን ሁሉ ለመክፈል ቁርጠኛ ነን” ብለዋል። ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና ተደራዳሪ ኀይሎች ለውይይት እንዲቀርቡ በማድረግ ረገድም በኀላፊነት እንሠራለን ብለዋል። ተወያዮቹ ተደራዳሪ ኀይሎች በመንግሥት አመኔታ እንዲኖራቸው መንግሥት ለውይይት ያለውን የጸና አቋሙን ማሳየት አለበትም ብለዋል።

የጸጥታ ችግሩ ኢኮኖሚያዊ እና ሰብዓዊ ኪሳራ ከማድረሱ ባሻገር የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ እና ወጣቱ የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዳይኾን ማድረጉን የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እያሱ ይላቅ አንስተዋል። በመኾኑም የታጠቁ ኀይሎች በተቋቋመው የሠላም ካውንስል በኩል ተቀራርበው ለውይይቱ እና ለድርድሩ ዝግጁ እንዲኾኑ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች አበክረው እንዲሠሩ ነው ያሳሰቡት። መንግሥት ለውይይት እና ለድርድር ቁርጠኛ መኾኑንም አረጋግጠዋል።

በዞኑ እገታን ጨምሮ ሌሎች ሕገ ወጥ ተግባራት እየተፈጸመ መኾኑን ያረጋገጡት ኀላፊው ሕገ ወጥ ተግባራት የፈጸሙ በርካታ ወንጀለኞች ላይ ሕጋዊ የእርምት እርምጃ መወሰዱንም ተናግረዋል።
በቀጣይም ሕግ የማስከበር ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ዘላቂ ሰላም የሚሰፍነው በመንግሥት ብቻ ሳይኾን በማኅበረሰቡ ተሳትፎ ጭምር መኾኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ቢክስ ወርቄ ጠቁመዋል።
በመኾኑም ሕዝቡ ይህን ተገንዝቦ ለሰላሙ እና ለልማቱ ዘብ እንዲቆም አሳስበዋል።

የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች እንዲፈቱ ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባም ነው ዋና አስተዳዳሪው ያስገነዘቡት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጥያቄ አለን በማለት ትጥቅ አንግበው የወጡ ኀይሎች ጥያቄዎቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ የምዕራብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር ጠየቀ።
Next articleከ230 ሚሊዮን ብር በላይ ጥቅል ካፒታል ያስመዘገቡ 16 አነስተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ መካከለኛ ደረጃ ተሸጋገሩ።