
ገንዳ ውኃ: ሐምሌ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር በወቅታዊ የሰላም እና ጸጥታ ጉዳይ ላይ ከዞኑ ከተወጣጡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር እየተወያየ ነው። በውይይቱ የምዕራብ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ ቢክስ ወርቄን ጨምሮ የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና እናቶች ተገኝተዋል።
በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት የክልሉን ሕዝብ ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየዳረገ መኾኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ቢክስ ወርቄ አንስተዋል። በመኾኑም ጥያቄ አለን በማለት ትጥቅ አንግበው የወጡ ኀይሎች ለሰላም እንዲቀርቡ እና ጥያቄዎቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል ዋና አሥተዳዳሪው። ለሰላም አበክረን በመሥራት የአማራን ሕዝብ ከሞት እና እንግልት መታደግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በአካባቢው እየተፈጸመ ያለው የእገታ፣ ዘረፋ እና ግድያ ወንጀል ማኅበረሰቡን እረፍት እየነሳ መኾኑንም አቶ ቢክስ አንስተዋል። የግል ጥቅመኞች መንገድ በመዝጋት የዜጎችን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲገታ እየሠሩ ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ማኅበረሰቡ እነዚህን ሕገወጥ ወንጀሎች ማውገዝ እና ወንጀለኞችን ለሕግ አጋልጦ መስጠት አለበት ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!