
ባሕር ዳር: ሐምሌ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ሀገራዊና በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ እየመከሩ ነው። በመድረኩ ላይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃን ጨምሮ ሌሎች መሪዎችና የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ተገኝተዋል።
አቶ አደም በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የውይይት መድረክ የቀጠለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በነበራቸው የውይይት መድረክ ቀጣይ ውይይቶች የሚደረጉ መኾኑን በገለጹት መሰረት ነው ብለዋል።
በመድረኩም በሀገራዊ እንዲሁም በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ጉዳዮች ያጠነጠኑ እና በቀጣይ ለሚደረግ ዋና መድረክ የሚቀርቡ አጀንዳዎች የሚለዩበት መኾኑን ጠቁመዋል። የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ ከዚህ በፊት በክልሎች በተደረጉ የውይይት መድረኮች የተጠቃለሉ ቁልፍ አጀንዳዎች መነሳታቸውን አስታውሰዋል። የነበሩት አጀንዳዎች ሀገራዊ ጉዳዮች፣ በመንግሥትና በፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም በተፎካካሪ እና በገዥ ፓርቲ የትብብር ማዕቀፍ መዘርጋት፣ በፖለቲካ ምህዳር ማስፋት፣ በሠላምና ደኅንነት፣ አካታች ሀገራዊ ምክክርና ሌሎችም ነበሩ ብለዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው በእነዚህና ተያያዥ አጀንዳዎች ዙሪያ የውይይት መድረኩ የሚቀጥል መኾኑን የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!