
ባሕር ዳር: ሐምሌ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ.ር) አነሳሽነት ከተገነቡ ጠቀሜታ ካላቸው የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል አንዱ ነው። ተመርቆ ለሥራ እና ለጎብኝዎችም ክፍት ኾኗል። ከየአካባቢው የተውጣጡ ጎብኝዎች ሪዞርቱን እየጎበኙት ነው። ጎብኝዎችም ከርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ጋር በልማት እና ሰላም ዙሪያም ውይይት አድርገዋል። ጎብኝዎቹ ባዩት ነገር መደነቃቸውን እና ኢትዮጵያ በዚህ ዘመን በአሁኑ ትውልድ በዓለም ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንደምትኾን ተስፋ እንደሰነቁባቸው ገልጸዋል።
ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጉብኝቱ የተሳተፉ አዛውንት ”ጎርጎራን ከዚህ በፊት አውቀዋለሁ፤ በርካታ ጉድለቶች ነበሩበት፤ አሁን ግን በቃላት መግለጽ የማይቻልበት የልማት ደረጃ ላይ ነው፤ መግለጽ የሚቻለው መጥታችሁ እዩት በማለት ብቻ ነው” ብለዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚገነቡት እና የሚታደሱ መዳረሻዎች ታሪኩን እና ባሕሉን በጠበቀ መልኩ መኾኑን ጠቅሰው ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያሳሰቡት አስተያየት ሰጪዎቹ ኅብረተሰቡም ከመተቸት እና አሻግሮ ከመመልከት ይልቅ መሪዎችን ሩቅ አሳቢ እንዲኾኑ ማገዝ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።
ከልማቱ በተጓዳኝ የተፈጠረውን ግጭት እና የሰላም እጦት ለመፍታት መንግሥት በኀላፊነት ከልብ መሥራት አለበት ተብሏል። ልማትም የሚቀጥለው ሰላም ሲኾን ነው ብለዋል። እንደ ልማቱ ሁሉ ለሰላማችን ትልቅ ሥራ መሠራት አለበት። እናቶች፣ አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎችም ለሰላሙ መሥራት አለባቸው በማለት ተናጋሪዎች አሳስበዋል። የጎበኘነውን አድንቀን መሄድ ብቻ ሳይኾን ባለ ሃብቶች ልማቱን እንዲያስፋፉ እና የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ የሰላምን ወሳኝነት ትኩረት እንስጥ ብለዋል።
ጎርጎራን መሰል በርካታ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ እና ቱሪስት በመሳብ የሀገር ምጣኔ ሃብትን የሚያሳድጉ የልማት ሥራዎችን ለመገንባት ሰላም አስፈላጊ ነው ሲሉ ነው አስተያየት ሰጪዎቹ በአጽዕኖት የተናገሩት። ጫካ ያሉ ወንድሞቻችን ልዩነቶቻቸውን በሰላም እና በውይይት ፈትተው ሁሉም በአንድ ልብ ወደ ልማት እንግባ ብለዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ወርቁ ኀይለማርያም በዞናቸው የሰላም ካውንስል ተቋቁሞ ኅብረተሰቡን በማወያየት ላይ መኾኑን ገልጸዋል። የመጣንበት የእርስ በእርስ ግጭት እንደማይጠቅመን አውቀን ችግሮችን በውይይት እንፍታ የሚል አቋም ተይዞ እየተሠራ ነውም ብለዋል።
የተጀመረው በሰላም የመወያየት ጅምር ተስፋ ያለው ሲኾን ቀድሞውንም ሰላም ፈላጊ የኾነው ሕዝብ ግጭቱ ከኑሮ ውድነቱ ላይ ተጨምሮ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረበት ስለኾነ የሰላም አማራጩን በእጅጉ የሚፈልገው እና የሚተባበርበት እንደሚኾን አመላክተዋል። ቁጭ ብላችሁ ችግራችሁን በሰላም ፍቱ በማለት ሕዝቡ ሲመክር እንደቆየ የተናገሩት አቶ ወርቁ በጦርነት የተጀመረ በጦርነት አይቋጭም ስለዚህ በውይይት እና በንግግር መፈታት ነው ያለበት ብለዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ ደግሞ በጣና ሐይቅ ዙሪያ በርካታ ሃብቶች እንዳሉ ዘርዝረው የተፈጥሮ ሃብታችንን በአግባቡ አውቀን በመጠቀም በፍቅር እና በሰላም መኖር እንችላለን ብለዋል። ከመጠላለፍ፣ ከጦርነት እና ግድያ ወጥተን ፍቅር እና ይቅር ባይነትን ጨምረንበት ከተጋገዝን እንደ ጎርጎራ ያሉ ፕሮጀክቶች በበርካታ ቦታዎች በመገንባት መጠቀም እንችላለን ነው ያሉት።
በአማራ ክልል የተቀሰቀሰውን የግጭት ችግር ለመፍታት የሰላም ካውንስሉ ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት እንዲፈቱ ላደረገው ጥሪ ዞኑ በትኩረት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። የሚፈለገውን ሰላም ለማምጣት የሰላም ካውንስሉ በገለልተኝነት እንዲሠራ ኀላፊነት የተሰጠው በመኾኑ ለስኬታማነቱ ኅብረተሰቡ ሰፊ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የታጠቁ ኀይሎችም ኢትዮጵያ ለሁላችንም የምትበቃ መኾኗን እንዲገነዘቡ፤ አንዳችን ለአንዳችን አለኝታ እንጂ ጠላት ባለመኾን የሰላም ካውንስሉን ጥሪ ተቀብለው ሰላም እንዲመጣ እና ሕዝቡ ያጣውን ሰላም እንዲያገኝ፤ በሚያገኘው ሰላም ልማቱን እንዲያፋጥን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስባለሁ ብለዋል አቶ ጥላሁን።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ጎብኝዎችን አወያይተዋል። አሁን ላይ እየለሙ እና ለሕዝብ ጥቅም እየሰጡ ያሉ ቦታዎች ከጸጋነታቸው ይልቅ በችግርነት ይታዩ የነበሩ አካባቢዎች ናቸው ብለዋል። በሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎችም ተመሳሳይ የልማት ሥራዎቶች እየተሠሩ መኾናቸውን አመላክተዋል። የሎጎ ሃይቅ እና የጎንደር ከተማ ፋሲልና አካባቢ የልማት ሥራም ቀጣይ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የጎርጎራ ፕሮጀክት በቢሊየኖች የሚቆጠር ብር ወጥቶበት መገንባቱን እና የፌዴራል መንግሥትም ለአማራ ክልል ሕዝብ እና መንግሥት ማስረከቡን ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል። ብዙ ፕሮጀክቶች ሢሠሩ የአካባቢውን ሥነ ምህዳር የሚያዛቡ እንደነበሩ የገለጹት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የጎርጎራ ግን ከተፈጥሮ የሚስማማ እና የአካባቢውን ታሪክ ጠብቆ መሠራቱን ተናግረዋል።
ባሕር ዳር እና ጎንደር የቱሪስት አካባቢዎች መኾናቸው እና በማዕከላዊነት የሚያገናኛቸው ጎርጎራ ሌላ ተጨማሪ የቱሪስት መስህብ ኾኖ እንደሚያገለግል፤ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር እና የአካባቢውን ገጽታም እንደሚገነባ ጠቅሰዋል። ታሪካችንን ከግጭት አውጥተን ላባችን አፍስሰን ልማትን ማረጋገጥ አለብን ያሉት ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ የጎርጎራ ፕሮጀክት የመንግሥት የልማት ፍላጎት ማሳያ ነው። የቀደምቶችን ታሪክ የበለጠ የማልማት ሥራ ነው። የዜጎችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የሚሠራ የመንግሥት ሥራም ነው ብለዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም፣ የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት እና በየአካባቢው የሚሠሩ ሥራዎች ታሪክን እየዘከሩ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል። መንግሥታቸውም ትላንትናን ከዛሬ፤ ዛሬን ከነገ በማስተሳሰር ለቀጣዩ ትውልድ ለማቆየት የሚተጋ መኾኑንም ተናግረዋል።
በልማቱ ሂደት የሚገጥሙ ችግሮችን መንግሥት በሆደ ሰፊነት ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው። ኅብረተሰቡ በማኅበራዊ ሚዲያ አሉቧልታ እየተደናገረ እንጂ መንግሥት ከመጀመሪያውም ችግሩን በሰላም ለመፍታት ይፈልጋል ነው ያሉት። ዛሬም ነገም የግጭቱ መቋጫ የሚኾነው ውይይት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ዛሬም ተፈታ ነገ የክልሉ ማኅበረሰብ የበለጠ ጉዳት ሳይደርስ በሰላም መፍታት እንደሚበጅ አሳስበዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ በ2017 በጀት ዓመት ዋና አጀንዳችን ልማት ነውና የግጭት አጀንዳችን መቋጨት አለበት ብለዋል። የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሌሎች አፍሪካውያን ጋር እኩል የልማት ጉዞ እንዲኖረው ሙሉ አቅም እና ጊዜያችን ለልማት ማዋል አለብን ነው ያሉት። ኅብረተሰቡም እንደ ሕዝብም ኾነ እንደ ቤተሰብ ለሰላሙ እንዲጥር ርእሰ መሥተዳድሩ አሳስበዋል።
መንግሥትም አዳዲስ ሃሳቦችን በመጨመር ጎርጎራ፣ ሎጎ ሐይቅ፣ መገጭ ግድብ፣ የፋሲል ግንብ ጥገና እና የመሳሰሉት ላይ ሃብት በማፍሰስ ለማልማት ይጥራል። ኅብረተሰቡም የልማቱ ተሳታፊም ተጠቃሚም ለመኾን ከመንግሥት ጎን እንዲሰለፍ ጠይቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!