
ባሕር ዳር: ሐምሌ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ10 ሺህ ሜትር እና በግማሽ ማራቶን የታወቀች ኢትዮጵያዊ ሯጭ ናት። እኤአ በ2003 ዓ.ም የዓለም ሻምፒዮና በ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሯ አስገኝታለች። በ2001 እና በ2005 የዓለም ሻምፒዮናም የብር ሜዳሊያ አሸንፋለች፡፡
በ2003 እና በ2004 ዓ.ም ደግሞ በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በ3 ሺህ ሜትር የወርቅ እና የብር ባለቤት ኾናለች፡፡ በ2003 ያገኘችው ሜዳሊያ በሴቶች ውድድር በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የዓለም የቤት ውስጥ ሜዳሊያ ነው፡፡
እ.ኤ.አ. በ2002 ዓ.ም በግማሽ ማራቶን የዓለም ሻምፒዮን ኾናለች። በ2003 ብር፣ በ2001 ነሐስ አሸንፋለች፡፡ በ2006 እና 2007 ዓ.ም ደግሞ በችካጎ የማራቶን አሸናፊ ናት፡፡
በበርካታ ውድድሮች ተሳትፋ በርካታ ድሎችን ያስመዘገበችው አትሌቷ ከ20 ጊዜ በላይ ሜዳሊያ ውስጥ ገብታለች፡፡ ከዚህም ውስጥ 11ዱ ወርቅ ነው፡፡ ይህቺ በዘመኗ እንደ ኮከብ አብርታ ለተተኪዎቿም አርዓያ የኾነችው ባለ ድል አትሌት ኮማንደር ብርሃኔ አደሬ ናት፡፡
አትሌት ኮማንደር ብርሃኔ በሀገር ውስጥ በ5 እና 10 ሺህ ሜትር በማሸነፍ ለዓለም አቀፉ መድረክ የበቃችው አንጎላ በተደረገ የ15 ኪሎ ሜትር ሩጫ ድሏን በማሟሽት ነበር፡፡ ከኬንያዎች እና ከእንግሊዛዊቷ ፓውላ ራድ ክሊፍ ብርቱ ፉክክርን አድርጋ ለኢትዮጵያ ድልን አስገኝታለች፡፡ የኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ እና የዓለም ክብረ ወሰኖችንም ሰባብራለች፡፡
በቡድን የተፎካካሪ ሀገርን አትሌት ካዳከሙ እና ከቀደሙ በኋላ ለግል አሸናፊነት የሚሮጥበት ዘመን አባል የነበረችው አትሌት ኮማንደር ብርሃኔ አደሬ በዙሪክ፣ በስቱጋርት፣ በኦስሎ እና በፓሪስ ሴንት ደኒስ ያገኘቻቸው ድሎች ያሳካቻቸው ክብረ ወሰኖቿ ኾነው ተመዝግበዋል፡፡
ብርሃኔ በዩኒሴፍ የሴቶች ትምህርት በጎ ፈቃድ አምባሳደር ኾናም ሠርታለች።
ይህቺ በዘመኗ እንደ እንቁ ያበራች እና ለተከታዮቿም አርዓያ የኾነች ኢትዮጵያዊ አትሌት የተወለደችው በዛሬዋ እለት ሐምሌ 14 ቀን 1968 ዓ.ም ነው፡፡
👉ሰዓሊ ሻምበል ለማ ጉያ
በኢትዮጵያ ስመ ጥር ከኾኑት የሥነ ስዕል ጠበብቶች ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ ገበሬ፣ መምህር እና እስከ ሻምበልነት ማዕረግ የደረሱ ወታደር ኾነውም ሀገራቸውን በአየር ኀይል መካኒክነት እንዳገለገሉ ይነገርላቸዋል፡፡ ቀጥለውም በስዕል ሙያ ተሰማርተው የስዕል ሥራዎቻቸውን በሀገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች አቅርበዋል፡፡
”የተፈጥሮ የአሳሳል ስልት ይጠቀማሉ” የሚባሉት ሰዓሊ ሻምበል ለማ ጉያ በፍየል እና በሬ ቆዳ ላይ የመሳል ጥበብን በመጠቀም የነገሥታትን እና የብሔረሰቦችን፣ የሴቶችን እና የገበሬዎችን ባሕላዊ አልባሳት ይስሉ እንደነበር ይነገርላቸዋል። ”ስዕል ያለ አስተማሪ” የተሰኘች የስዕል ማስተማሪያ መጽሐፍም አዘጋጅተዋል፡፡ በፍየል ቆዳ ላይ የሚስሏቸው ስዕሎች እንደገና ፎቶ ተነስተው ሲታዩ ሕይወት ያላቸው የሚመስሉ እና ገዝፈው የሚነሱ ናቸው፡፡
በሙያቸው እና በሰብዕናቸው ዓለምን አሥተምረዋል፡፡ በሰሜን አሜሪካ፣ እና በደቡብ አፍሪካ፣ ተጋብዘው የሀገራቸውን ክብር ከፍ አድርገዋል፡፡ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷቸዋል። 10 ሺህ የሚኾን የጥበብ ሥራ እንዳፈሩ የሚነገርላቸው የጥበብ ሰው በአዲስ አበባ፣ በደብረ ዘይት፣ በአስመራ፣ በናይጄሪያ፣ በሴኔጋል፣ ሥራቸውን አቅርበዋል፡፡ በሰሜን አሜሪካ ኒውዮርክ ያሳዩትን ዓውደ ርዕይ የከፈቱት የወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን ነበሩ፡፡
”ቋንጣ” የሚል ርዕስ የሰጧት የሥዕል ሥራቸውም የአፍሪካን የሃብት ምዝበራ እና ቅርምት ታሳያለች መባሏ እርሳቸውም ይህንኑ ማረጋገጣቸው ይነገራል፡፡ ሁለገቡ ባለሙያ፣ የስዕል ጥበበኛ፣ የሀገር አምባሳደር የተወለዱት ነሐሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም በያዝነው ሳምንት ነበር፡፡
#ሳምንቱበታሪክ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!