
ባሕር ዳር: ሐምሌ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከዓመታት በፊት በጎንደር ከተማ ውስጥ ያጋጠመኝን አንድ ዕውነታ ልንገራችሁ፤ ፒያሳ በሚባለው አካባቢ አስፋልት እያቋረጥኩኝ እያለሁ በትራፊክ ፖሊስ ፊሽካ ተጠራሁ። መኪና የሌለኝን እግረኛ ትራፊኩ ለምን እንደሚጠራኝ ግራ ቢገባኝም ወደ ትራፊኩ ሄድኩኝ። “ለምን ዜብራ ባልኾነ ቦታ ታቋርጣለህ?” ትራፊኩ ጠየቀኝ።
“በዜብራ የማቋረጥ ግዴታ ያለብኝ ስላልመሰለኝ ነው” ብዬ እውነታውን ለትራፊኩ ነገርኩት። የትራፊክ ፖሊሱ ለትራፊክ አደጋ መንስኤዎቹ አሽከርካሪዎች ብቻ አለመኾናቸውን በመግለጽ ጥፋቴን አስረዳኝ። በጥፋቴም መሠረት 10 ብር በደረሰኝ እንደምቀጣ፣ ገንዘብ ካልያዝኩ ደግሞ ለ30 ደቂቃዎች የመቆም ቅጣት እንዳለብኝ ገለፀልኝ። ጥፋቴን ባለማወቅ የፈፀምኩኝ ቢኾንም በ10 ብር ለመቀጣት ተስማማሁ። ፖሊሱ ዳግመኛ እንዳላጠፋ መክሮኝ ምንም ሳይቀጣኝ አሰናበተኝ። እኔ ግን ከዚያ ጊዜ በኋላ መንገድ ያለ ዜብራ አላቋርጥም።
ይሄንን ምሳሌ ያነሳሁት በባሕርዳር ከተማ ለከተማዋ ውበት እንቅፋት የኾኑ ሕገ ወጥ የመንገድ ላይ ንግድ፣ ሕገ ወጥ ግንባታ እና ሌሎችም ሕገ ወጥነቶች መብታቸው የመሰላቸው ብዙ ዜጎች ስላሉ ነው። ለእነዚህ ዜጎች ከተማ አሥተዳደሩ ሕገ ወጥ መኾናቸውን ግንዛቤ በመፍጠር ለከተማዋ ድምቀት እና ውበት ተባባሪ ማድረግ ይገባል። አንድ ነዋሪም ከተማዋ ላይ ቆሻሻ ጥሎ ሲገኝ እና ሲነገረውም እንደኔ ጥፋቴ ነው ብሎ ማመን ግድ ይለዋል። የታሸገ ውኃ ጠጥቶ ፕላስቲኩን የትም መወርወር፣ ፍራፍሬዎችን በልቶ ልጣጩን የትም መጣል እና በአጠቃላይ ደረቅ ቆሻሻዎችን በአግባቡ ማስወገድ አለመቻል ተጠያቂ ሊያደርገን ይገባል። በተለይም የክረምቱን መግባት ተከትሎ ቆሻሻዎቻችንን የምናስወግደው በውኃ ማፋሰሻ ቦዮች ውስጥ ከኾነ ጥፋታችን ድርብርብ ይኾናል።
ባሕርዳር ከተማ ውብ ብትኾንም ውበቷን የሚያጎድፉ ችግሮችም አልፎ አልፎ ይስተዋላሉ። የዚች ውብ ከተማ መገለጫዎች በርካታ ቢኾኑም ብዙዎቻችን ግን ዘንባባዎቿ፣ የጣና ሐይቅ እና ለውበቷ ያገለደመችውን የዓባይ ወንዝ ብቻ ጠቅሰን እናቆማለን። የውስጥ ለውስጥ ጌጠኛ መንገዶች፣ የአስፋልት መንገዶች፣ የተከለሉ አረንጓዴ ሥፍራዎች፣ ሕንፃዎቿ እና ተሽከርካሪዎቹ ሳይቀሩ ጌጧ መኾናቸውን ልብ አንልም። ባሕር ዳር ውበቷ እንዳይኮሰምን ጥረት ከሚያደርጉት ውስጥ የከተማዋ ጽዳት ሠራተኞች ሚናቸው የጎላ ነው:: እነዚህ በከተማ አሥተዳደሩ ተቀጥረው የሚሠሩ የጽዳት ባለሙያዎች ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ ባመዛኙ የከተማዋ ነዋሪዎች ኀላፊነት በጎደለው መልኩ የጣሏቸውን ቆሻሻዎች በትጋት ያፀዳሉ።
የጽዳት ባለሙያዎቹ በሌሊት ተነስተው ባሕር ዳርን ሲያስውቡ አልፎ አልፎ ለተሽከርካሪ አደጋ ሲጋለጡም ይስተዋላል። የሚለብሷቸው ቱታዎች፣ የእጅ ጓንቶች፣ ጫማቸው፣ በአፍ እና በአፍንጫቸው ላይ የሚያጠልቁት ጭምብል ሳይቀር ራሳቸውን ከቆሻሻ ለመከላከል የሚያስችል አለመኾኑን ለመታዘብ ችያለሁ።
በጽዳት ሥራ ላይ የተሰማሩ አንዳንድ የግል ድርጅቶችም የባሕር ዳርን ደረቅ ቆሻሻ ለማስወገድ ሚናቸው ጉልህ ቢኾንም አንዳንድ ጊዜ ከየሰፈሩ የሚያነሱትን ቆሻሻ በወቅቱ ባለማንሳታቸው አካባቢውን ለመጥፎ ሽታ ይዳርጉታል። መጥፎው ሽታ በጤና ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በመለስ ለከተማዋ ነዋሪዎችም ኾነ ባሕር ዳርን ለመጎብኘት ለሚመጡ እንገዶች ምቾት አይሰጥም። ለከተማዋ ውበት ተብሎ በተተከለ ሳር ላይ መራመድ፣ በአረንጓዴ ሥፍራዎች ላይ መተኛት፣ የተተከሉ አትክልቶችን መቁረጥ እና ሌሎችም እኩይ ተግባሮቻችን ባለማወቅ ነው ተብለው ብቻ የሚታለፉ ሳይኾን በሕግ ሊያስጠይቁንም ይገባል።
አንዳንድ የመኪና ማጠቢያዎች ለራሳቸው ከሚያገኙት ጥቅም ውጭ ለከተማዋ ውበት አለመጨነቃቸው የምር ያሳዝናል። የመኪኖችን የተቃጠለ ዘይት በእግረኞች መንገድ ላይ መድፋታቸውም ኾነ መኪኖችን ያፀዱበትን ጨርቅ በየመንገዱ ላይ መጣል “ከራስ በላይ ነፋስ” ለሚለው ግብዝነት የሚዳርጋቸው ስለኾነ ከስህተታቸው ቢማሩ እላለሁ።
አንዳንድ አሽከርካሪዎች እና ረዳቶቻቸውም በየአስፋልቱ ዳር በሚያሳድሯቸው መኪናዎች ጎማ ስር መሽናታቸው ለኅብረተሰብ ጤና ጠንቅ መኾኑን ሊገነዘቡት ይገባል፤ ከስህተታቸውም መማር ይኖርባቸዋል፡፡ ለከተሞች ውበት የነዋሪዎቻቸው ድርሻ ከፍተኛ ቢኾንም ባለሃብቶችም የማይናቅ አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርባቸዋል። ለአብነትም የጣና ሐይቅን እና የዓባይ ወንዝ ዳሮችን በማስዋብ ለጎብኚዎቹ ምቹ ማድረግ የብዙዎችን ጥረት ይጠይቃል። ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃዎችን ለከተማዋ ማቅረብም ስምን እና ግብርን በደማቁ ለማጻፍ ይጠቅማል።
የከተማዋ ውስጥ አደባባዮች ከተማዋን እና ክልሉን የሚገልጽ ውበት እንዲላበሱ ማድረግም የባለሃብቶችን፣ የሥነ ጥበብ ሙያተኞችን፣ የባሕል እና ቱሪዝም ሙያተኞችን እንዲሁም የሌሎችንም ትብብር ይጠይቃል። “ውቧ” እያልን የምናወድሳት ባሕር ዳር የበለጠ ውብ እንድትኾን ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል።
በከተማችን ውስጥ አፍንጫችንን በእጃችን የሚያሲዘን መጥፎ ሽታ ሳይኾን ወደ ሳንባችን የምናስገባው ንፁህ አየር እንዲኖር ሁላችንም እንመኝ፤ መመኘት ብቻም ሳይኾን የዜግነት ግዴታችን እንደኾነ እናስብ፡፡
የባሕርዳርን ውበት የሚያጎድፉ ችግሮችን በትዝብታችን ለመጥቀስ ሞክረናል ኾኖም ግን እያንዳንዳቸው ችግሮች ትኩረትንና መፍትሔን የሚሹ ናቸው።
ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!