በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና የአፍር ክልል ሕዝብን አብሮነት ለማስቀጠል መሥራት እንደሚገባ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገለጸ።

15

ከሚሴ: ሐምሌ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና በአፋር ክልል የዞን አምስት አሥተዳደር በአፋር ክልል ደዌ ወደራጌ ወረዳ ውይይት አካሂደዋል።

በውይይት መድረኩ የደዌ ወደራጌ ዋና አሥተዳዳሪ መሐመድ ቦዳያ ሁለቱ አጎራባች ሕዝቦች ለዘመናት በአንድነት የኖሩ በመኾኑ በቀጣይ ሁለቱ አጎራባቾች በልማት እና በፀጥታ ጉዳዮች በትብብር ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።

በአማራ ክልል የደዌሀረዋ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ መሐመድሷቢር ሀጂ በሁለቱ አጎራባች አዋሳኝ አካባቢዎች ሁለቱን ሕዝቦች ለማጋጨት የሚሠሩ የጥፋት ኀይሎች ላይ በጋራ የሕግ ማስከበር ተግባር በቀጣይ እንሠራለን ነው ያሉት።

የአፋር ክልል ዞን አምስት ምክትል አሥተዳዳሪ አሊ ሱልጣን ሁለቱ የአፋር እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሕዝቦች የተዋለዱ እና የተዛመዱ በመኾኑ አብሮነታቸውን ለማስቀጠል ሕዝብን ያሳተፈ ሥራ ወደፊት እንሠራለን ብለዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ በሁለቱ አጎራባች አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ኀይሎችን የጋራ የሕግ ማስከበር ሥራ በመሥራት አካባቢውን በዘላቂነት ለማጥራት በትብብር ለመሥራት መግባባት መፈጠሩን አስረድተዋል።

ለሁለቱ ሕዝቦች ባስተላለፉት መልዕክት ጽንፈኝነት ብሔርም ድምበርም የለውም በማለት በሁለቱ አጎራባች አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኞችን መላው የሁለቱ አጎራባች ሕዝቦች ከመንግሥት ጋር በመኾን ሊታገላቸው ይገባል ብለዋል።

የሁለቱ አጎራባች የመድረኩ ተሳታፊዎች በወረዳው የችግኝ ተከላም አካሂደዋል።

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሂም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ችግኞችን በመትከልና የደን ሽፋንን በማሳደግ የተጎዱ መሬቶችን ለመጠገን መረባረብ ይገባል” አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
Next articleጽዱነት ለራስ ነው!