“ትውልዱ በላቡ ከድህነት በመውጣት ራሱን የሚመግብ ማኅበረሰብ እንዲኾን መሥራት ያስፈልጋል” የደቡብ ወሎ ዞን

15

ደሴ: ሐምሌ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የምግብ ክፍተት ለመሙላት ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ፣ሉዓላዊነት እና ክብር በሚል መሪ መልዕክት በደቡብ ወሎ ዞን የተግባር ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን በዓመት ከ700 ሺህ በላይ ሕዝብ የምግብ ዋስትና(ሴፍቲኔት) ተጠቃሚዎች ናቸው።እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች የምግብ ክፍተትን ለመሙላት እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የዞኑ ግብርና መምሪያ መረጃ ያመላክታል፡፡

ይህንን የምግብ ክፍተት ለመሙላት ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነት እና ክብር በሚል መሪ መልዕክት በዞኑ ቃሉ ወረዳ የተግባር ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አህመድ ጋሎ በበጀት ዓመቱ ከ2 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት መታረስ የሚገባው እና ያልታረሰ መሬት እንደተለየ ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ ከ400 ሄክታር በላይ የሚኾነውን ለማልማት ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።

መምሪያ ኀላፊው በአግባቡ ጥቅም ሳይሰጡ የቆዩ የግብርና፤ የትምህርት፤ የጤና እና መሰል ተቋማት በኢንቨስትመንት እና በከፍተኛ ተቋማት ተይዘው የነበሩ እና የወል መሬቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

ከተለዩት ውስጥም 100 ሄክታሩ እስካሁን በዘር መሸፈኑን የጠቆሙት አቶ አህመድ አስፈላጊው ግብዓት እና ቴክኖሎጂ እንደቀረበም ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አሊ መኮነን ትውልዱ በላቡ ከድህነት በመውጣት የሚያድግ እና ራሱን የሚመግብ ማኅበረሰብ እንዲኾን መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

በእርዳታ ስም ከሚመጡ እጅ ጠምዛዥ አስተሳሰቦች ለመውጣት ሠርቶ ራስን መቀየር ተገቢ መኾኑን ያነሱት ዋና አሥተዳዳው ለዚህም ሰፊ መሬት፣ በቂ ጉልበት፣ የከርሰ ምድር እና ገጸ ምድር ውኃ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

ያለውን ሃብት በአግባቡ አልምቶ ተጠቃሚ ለመኾን የሕዝብ እና የመሪ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግም ነው ያነሱት አቶ አሊ፡፡

ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነት እና ክብር በሚል መሪ መልዕክት በተጀመረው ንቅናቄም የማኅበረሰቡን የምግብ ክፍተት ለመሙላት በትኩረት እንደሚሠራ ጠቅሰዋል፡፡

ተግባሩ በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች እንደሚተገበርም አንስተዋል፡፡

በተቋማት ተይዞ እስካሁን በአግባቡ ያለማ መሬትን ለማልማት ተግባራዊ ሥራ መጀመሩ እንዳስደሰታቸው የቃሉ ወረዳ እና አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡

በዚሁ መርሐ ግብር የሚመረተው ምርት በወረዳ ደረጃ ተከዝኖ የምግብ ክፍተትን ለመሙላት እንደሚውል ተገልጿል፡፡

ዘጋቢ:- ደጀን አምባቸው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከፒያሳ እስከ ጃን ተከል ዋርካ የተጀመረዉ የኮሪደር ልማት በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቅ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።
Next articleየብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሀገርን ማረጋጋት እና ማፅናት ያስቻሉ የመረጃ ስምሪቶች እና የኦፕሬሽን ሥራዎች ማካሄዱ ተገለጸ።