ከፒያሳ እስከ ጃን ተከል ዋርካ የተጀመረዉ የኮሪደር ልማት በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቅ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

58

ጎንደር: ሐምሌ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ገልጿል።

ከተማ አሥተዳደሩ ውጥኑ ግቡን እንዲመታ በልማቱ የተሰማሩ ባለሙያዎችን እና ሠራተኞችን እያበረታታ ነው።

የጎንደር ከተማ አስሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ እንዳሉት ከተማዋ የቱሪስት መዳረሻ እንደመኾኗ ጎንደርን ማስዋብ እና ለጎብኝዎች ምቹ ማድረግ ያስፈልጋል።

በልማቱ የሚሳተፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የቀን ገቢ ከማግኘት ባለፈ ከተማቸዉን የመቀየር እና የታሪክ አሻራ ማሳረፍ መኾኑን ዐውቀው እና በርትተዉ እንዲሠሩም ጠይቀዋል።

የተጀመረዉ ልማት እንዲጠናቀቅ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የበኩሉን እንዲወጣ ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል።

ከፒያሳ እስከ ጃን ተከል ዋርካ የተጀመረዉ የኮሪደር ልማት በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባዉ በቀጣይም ከራስ ግንብ እስከ ብልኮ (አርበኞች አደባባይ) በከተማዉ አቅም ለመሥራት እቅድ ተይዟል ብለዋል።

በኮሪደር ልማቱ የሥራ እድል ከተፈጠረላቸዉ ግለሰቦች መካከል ወጣት አግኝቸዉ ሙጨ እና ስንቄ መለሰ በተሰማሩበት ሥራ የዕለት ገቢ ከማግኘት ባሻገር በከተማዋ የገፅታ ግንባታ ላይ በመሳተፋቸው ደስታን እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዲስ አለማየሁ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በጫካ ፕሮጀክት አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ።
Next article“ትውልዱ በላቡ ከድህነት በመውጣት ራሱን የሚመግብ ማኅበረሰብ እንዲኾን መሥራት ያስፈልጋል” የደቡብ ወሎ ዞን