
ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ያቀረቡት ጥሪ ሦስተኛ ምዕራፍን ተከትሎ ከልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ ወጣቶች በጫካ ፕሮጀክት አረንጓዴ አሻራቸውን አስቀምጠዋል።
የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያኑ አረንጓዴ አሻራቸውን ከማሳረፋቸው በተጨማሪ በጫካ ፕሮጀክት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችንና የኮሪደር ልማትን ተመልክተዋል።
መርሐ ግብሩ የጥሪው ብሔራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ በኾነው ቱሪዝም ሚኒስቴርና በኮሚቴው አስተባባሪው ኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የተዘጋጀ መኾኑን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አለምፀሀይ ጳውሎስ፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አቅናውን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ጥሪውን ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት ለሚመጡ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የተሰናዱና ይፋ የተደረጉ መርሐ ግብሮች እስከ ጥቅምት መጀመሪያ ድረስ የሚቀጥሉ መሆኑ ይታወቃል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!