
ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለሁለት ተከታታይ ቀናት በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት ሲካሄድ የነበረው የ2016 በጀት ዓመት የማጠቃለያ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ 6ተኛው የጋራ ምክክር መድረክ ተጠናቅቋል፡፡
በጋራ የምክክር መድረኩ የ2016 በጀት ዓመት የክልል፣ ከተማ አሥተዳደርና የፌዴራል ተቋማት አደረጃጀት ኮሚሽን ሪፖርት፣ የኮሚሽኑ የተጠቃለለ የግምገማ ሪፖርት እና የ2017 በጀት ዓመት መሪ እቅድ ቀርቦ በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በጋራ የምክክር መድረኩ ማጠቃለያ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ስምምነት የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ሰላማዊት ዳዊት ከክልል፣ ከተማና ፌዴራል ተቋማት ኮሚሽን ሰብሳቢዎች ጋር የፊርማ ሥነ-ሥርዓት አድርገዋል።
ኮሚሽኑ በ2016 በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የኮሚሽን መዋቅር እና አስተዋጽኦ ላደረጉ ባለድርሻ አካላትና ግለሰቦች ዕውቅና ተሰጥቷል፡፡
በዕውቅናና ምሥጋና መርሐ-ግብሩ የተገኙት የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ በ2016 በጀት ዓመት የፓርቲው የኢንስፔክሽንና የሥነ-ምግባር ኮሚሽን ውጤታማ መኾኑን አንስተዋል።
ኮሚሽኑ ውጤታማ እንዲኾን ያስቻሉ ሦስት ምክንያቶችንም አንስተዋል፤ ጠንካራ የፓርቲ መዋቅር መፈጠሩ፣ የኮሚሽኑ አባላትና መሪዎች ተንቀሳቅሰው መሥራት መቻላቸው እና የኮሚሽኑን ተልዕኮ ለመወጣት ማመን፣ መደገፍና መተግበር በመቻሉ ነው ብለዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት ኮሚሽኑ “ጠንካራ ኢንስፔክሽን ፤ ለጠንካራ ፓርቲ” በሚል በጀመረው ንቅናቄ የፓርቲው የፖለቲካ ጥራት እንዲረጋገጥ፣ ሥነ-ምግባር እንዲሻሻል፣ አሠራሮች እንዲጠበቁ፣ በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲው አደረጃጀቶች እንዲጠናከሩ እና በፓርቲው ሀብትና ንብረት ላይ የሚደረገው ኢንስፔክሽን ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ማሳሰባቸውን ከፓርቲው ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!