“በተመረቅንበት የሙያ መስክ ሥራ ፈጣሪ እንጅ ሥራ ጠባቂ አንኾንም” ተመራቂ ተማሪዎች

24

ገንዳ ውኃ: ሐምሌ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ የሚገኘው የገንዳ ውኃ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ሲያሠለጥናቸው የነበሩ ሠልጣኞችን አስመርቋል።

የገንዳ ውኃ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ ዲን አዲሱ ጫኔ ኮሌጁ በደረጃ አራት በ11 የሙያ መስኮች 237 ተማሪዎችን ማስመረቁን ተናግረዋል።

ኮሌጁ ከተመሠረተ ጀምሮ ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 4 በመደበኛው እና በማታው መርሐ ግብር በማሠልጠን በርካታ የተማረ የሰው ኀይል እያፈራ መኾኑንም አቶ አዲሱ አስታውሰዋል።

ኮሌጁ ከመደበኛ ሥራው በተጨማሪ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የኢንዱስትሪ ኤክስቴሽን አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችን እና የፈጠራ ሥራዎችን በማስተዋወቅ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የገንዳ ውኃ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አብዱልከሪም ሙሐመድ ተመራቂዎች በኮሌጁ ያገኙትን ንድፈ ሃሳብ ከተግባር ጋር በማቀናጀት ሕዝብ እና መንግሥትን በቅንነት እንዲሁም በታማኝነት ማገልገል ይገባል ብለዋል።

ተመራቂዎች ከመንግሥት ሥራ ጠባቂነት ወጥተው ሥራ ፈጣሪ እና ተጠቃሚ መኾን እንዳለባቸውም ከንቲባው አሳስበዋል።

ዞኑ ለበርካታ የተማሩ ወጣቶች ሠፊ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ እንዳለው የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ ቢክስ ወርቄ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጅ ያለውን ሃብት በመጠቀም ረገድ ሠፊ ክፍተቶች እንዳሉ ነው ያነሱት።

ሃብቱን ጥቅም ላይ ለማዋል እና ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የዛሬ ተመራቂ ተማሪዎች ሀገራዊ ኀላፊነት አለባችሁ ብለዋል።

ሠልጣኞች በሥልጠና ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀት እና ክህሎት ከአካባቢው ጸጋ ጋር በማቀናጀት ሥራ ፈጥረው ራሳቸውን እና አካባቢያቸውን መጥቀም እንዳለባቸው ዋና አሥተዳዳሪው አሳስበዋል።

ተመራቂ ተሾመ ገረመው በተመረቀበት የሙያ መስክ ሥራ በመፍጠር ራሱን፣ ቤተሰቡን እና ሀገሩን መጥቀም እንደሚችል ለአሚኮ ገልጿል።

ሌላኛዋ ተመራቂ አብባ ሐብቴ ከመንግሥት ሥራ ጠባቂነት ይልቅ በኮሌጁ ባገኘችው ዕውቀት እና ክህሎት ሥራ በመፍጠር ራሷን እና ሀገሯን ለማገልገል ቁርጠኛ መኾኗን ተናግራለች።

የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጁ በቀጣይ ዓመት ወደ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እንደሚያድግም ተገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሁለቱ ወገኖች ችግሩን ለመፍታት ውይይት እንዲያደርጉ መንገድ ለማመቻቸት የሚያስችል ምክክር እያደረጉ መኾናቸውን የሰላም ካውንስሉ አባላት አስታወቁ፡፡
Next articleበራያ ቆቦ ወረዳ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እየተከናወነ ነው።