
ደብረ ማርቆስ: ሐምሌ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በውይይት መድረኩ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ የሰላም ካውንስል አባላት በክልሉ ያጋጠመው የሰላም እጦት እያስከተለ ያለው ችግር እንዲያበቃ ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
ሰላም እንዲሰፍን ኅብረተሰቡ ከቀበሌ ጀምሮ ያነሳቸውን ጥያቄዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት።
የሰላም ካውንስሉ አባላት ፍፁም ገለልተኛ ኾነው የታጠቁ ኀይሎች ወደ ውይይት እንዲመጡ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
የሰላም ካውንስል አባላት በውይይቱ ሃሳቦችን በሚገባ በማንሳት እስካሁን የሄዱበትን ርቀት በመገምገም የቀጣይ ተግባራትን ግልጽ በኾነ መልኩ ማስቀመጥ ይገባቸዋል ነው ያሉት።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን እና የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የሰላም ካውንስል ሠብሣቢ በቀለ መንግሥት የሰላም ካውንስሉ ሕዝብ የጣለበትን አደራ ለመወጣት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
የሰላም ካውንስል አባላት የሕዝቡ እንግልት እና ሰቆቃ እንዲያበቃ በኀላፊነት ስሜት እንዲሠሩ አሳስበዋል።
ሕዝቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሰላም እንዲተጋ እና የካውንስሉን ተልዕኮ እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይቱ ላይ ከምሥራቅ ጎጃም ዞን እና ከደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የተውጣጡ የሰላም ካውንስል አባላት፣ የሥራ ኀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!