
ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ለጎንደር ከተማ ሕዝብ ተጠቃሚ የሚኾንበት እና ታሪኩን የሚመጥን የልማት ሥራዎች እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ የአካባቢው ማኅበረሰብ ሰላሙን ማስጠበቅ እንደሚገባው ገልጸዋል።
የሚሰሩ ፕሮጀክቶች የሕዝብን ተሳትፎ የሚጠይቁ በመኾኑ ኅብረተሰቡ የራሱን አሻራ እንዲያስቀምጥ አሳስበዋል።
“የጋራ ታሪካችን የኾነው የፋሲል አብያተ መንግሥት ጥገና መጀመሩን ተመልክቻለሁ” ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
የመገጭ ግድብ ተስፋ ያለው መኾኑን በጉብኝቱ መመልከታቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ ለመስኖ ልማት እና ለንፅህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት የሚያግዝ መኾኑን ገልጸዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በበኩላቸው ባለፉት አምስት ዓመታት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ የሥነ-ምህዳር እና በአየር ንብረት በመጠበቅ ከፍተኛ ሚና መኖሩን ገልጸዋል።
አረንጓዴ አሻራ ሰውን እና ተፈጥሮን በማገናኘት በኩል ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በክልሉ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል በንቅናቄ እየተሠራ መኾኑን ዶክተር ድረስ ገልጸዋል።
አረንጓዴ አሻራ የምድር ጌጥ ብቻ ሳይኾን የሕይዎታችን ዋስትና የአየር ንብረት በመጠበቅ ሰው እና ተፈጥሮን በማገናኘት በኩል ትልቅ ሚና አለው ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ ናቸው።
በከተማ ደረጃ 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል በንቅናቄ እየተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ መመሪያ የተሰጠባቸው ፕሮጀክቶች ለመከታተል እና የአረንጓዴ አሻራን ለማስቀመጥ ለተገኙት ለገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሀይ በጎንደር ከተማ አስተዳደሩ ስም ምስጋና ማቅረባቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!