
ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በስፔን ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት የኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍት ክፍል መከፈቱን የአብርኾት ቤተ መጻሕፍት ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ውብአየሁ ማሞ አስታውቀዋል፡፡
በስፔን ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ቅጥር ግቢ የተደራጀው የኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍት ክፍል የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባሕል እና ቋንቋ ለዓለም ለማስተዋወቅ እንዲረዳ መደራጀቱንም ነው የገለጹት፡፡
መጻሕፍቱን በስፔን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሚገባ እንዲጠቀሙባቸው አመች በኾነ የዲጂታል መተግበሪያዎች ሳይቀር መገኘት እንደሚችሉም ነው የተናገሩት፡፡
በፈረንጆቹ የዘመን ቀመር 1711 ላይ የተመሠረተው ታሪካዊው የስፔን ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ከ26 ሚሊዮን በላይ መጻሕፍትን በመያዝ በዓለም ከሚገኙ ስመ ጥር ቤተ መጻሕፍት ተርታ የሚሰለፍ መኾኑም ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ እና ስፔን ያላቸውን መልካም ግንኙነት መሠረት በማድረግ በሀገሪቱ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት የተደራጀው የኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍት ክፍል የሁለቱን ሀገራት የቆየ ወዳጅነት ይበልጥ ያጠናክረዋል ብለዋል፡፡
የአብርኾት ቤተ መጻሕፍት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከአውሮፓ ኅብረት እና ትብብር ተጠሪ ጉሌርሞ ኢስክቫኖ ጋር በመተባበር ኢትዮጵያውያን የስፓኒሽ ቋንቋ በነፃ እንዲማሩ መግባባት ላይ ተደርሷልም ነው ያሉት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!