ከ390 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በሰሜን ወሎ ዞን የተገነቡት የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ::

29

ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሰሜን ወሎ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 42 የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለሕዝብ አገልግሎት መብቃታቸውን የዞኑ ቤቶች እና መሠረተ ልማት መምሪያ አስታውቋል።

ለአገልግሎት የበቁት 42 ፕሮጀክቶች በዞኑ በከተማ እና ገጠር ለመገንባት በዕቅድ ከተያዙት 95 ፕሮጀክቶች መካከል መኾናቸውን መምሪያው ገልጿል።

የመምሪያው የመሠረተ ልማት ቡድን ተወካይ ዘርትሁን አሸብር እንደተናገሩት ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ከበቁት መካከል 72 ኪሎ ሜትር የመንገድ ከፈታ፣ 32 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ግንባታ እና 44 ኪሎ ሜትር የመብራት ዝርጋታ ይገኙበታል።

እንዲሁም 38 ኪሎ ሜትር የቧንቧ ውኃ መስመር ዝርጋታ እና ጎርፍን መከላከል የሚያስችሉ 19 ኪሎ ሜትር የተፋሰስ ሥራዎች እንደሚገኙበት አስረድተዋል።

አጠቃላይ ለፕሮጀክቶች ግንባታ ማስፈጸሚያ የተመደበው ከ390 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ እንደኾነ ጠቅሰው ቀሪዎቹ ፕሮጀክቶች እስከ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሠራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ለፕሮጀክቶቹ ግንባታም ኅብረተሰቡ በጉልበት፣ በገንዘብ እና በዕውቀት 85 ሚሊዮን ብር የሚገመት ገንዘብ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።

የመርሳ ከተማ ነዋሪ አቶ ያሲን ዳውድ በአዲስ የተቋቋመው መንደራቸው መሠረተ ልማት እንዲሟላለት ሲጠይቁ እንደቆዩ አስታውሰዋል።

ዘንደሮ የጠጠር መንገድ፤ የመብራት እና የውኃ መስመሮች ተዘርግተውላቸው እየተጠቀሙ መኾኑን ተናግረዋል።

በሐብሩ ወረዳ የውርጌሳ ከተማ የሞላ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አያልነሽ ተሾመ በንጹህ መጠጥ ውኃ ችግር ከወራጅ ወንዝ ይጠቀሙ እንደነበር ተናግረው አሁን ላይ የቧንቧ ውኃ መስመር በአካባቢያቸው በመዘርጋቱ የንጹህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው በሰሜን ወሎ ዞን ባለፈው ዓመት በ240 ሚሊዮን ብር በጀት የ88 ፕሮጀክቶች ግንባታ መከናወኑን የዞኑ ቤቶች እና መሠረተ ልማት መምሪያ አመልክቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ150 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥ ምርት ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡
Next articleየሰቆጣ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በቀን እና በማታው መርሐ ግብር ያሠለጠናቸውን 65 ሠልጣኞች አስመረቀ።