ከ150 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥ ምርት ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

33

ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሀገሪቱ ለውጭ ምንዛሬ የሚቀርቡ ገበያ ተኮር ምርቶች በምዕራብ ጎንደር ዞን በስፋት ይመረታሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ የሰሊጥ ምርት ነው።

በምዕራብ ጎንደር ዞን በ2016/17 የምርት ዘመን በተያዘው የመኸር ወቅት ከ150 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥ እየለማ መኾኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡

ከዘርፉ አምራቾች መካከል በመተማ ከተማ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር መሀመድ ተማም በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም ከአንድ ሄክታር ያገኙት ከነበረው የሰሊጥ እና ሌሎች ሰብሎች ምርት በአሁኑ ወቅት የግብርና ባለሙያዎች በሚያደርጉላቸው ድጋፍ እና በሚጠቀሙት የተሻሻሉ አሠራሮች ምርታቸውን አንዳሳደጉ ተናግረዋል።

የተሻለ ምርት የሚሰጥ ዘር እና ማዳበሪያን መጠቀም በመቻላቸው የሚያገኙት ምርት እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ነዋሪ የኾኑት በአምራች እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩት ባለሃብት አቶ ጉምቢ ጌታ ናቸው።

በዘንድሮ የመኸር ወቅትም የበለጠ ተጠቃሚ ለመኾን 150 ሄክታር መሬት ሰሊጥ እና ጥጥ ማልማታቸውን ነግረውናል። ከአምናው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁም ገልጸዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አንዳርጌ ጌጡ ለአሚኮ እንደገለጹት በሰሊጥ እየለማ ያለው መሬት ከታቀደው በ26 ሺህ ሄክታር ይበልጣል።

በባለሃብቶች እና አርሶ አደሮች እየለማ ካለው መሬትም ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ጠቅሰው ምርቱንም ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ገቢ የሚያስገኝ መኾኑን ተናግረዋል።

የተሻለ ምርት የሚሰጡ የሰሊጥ ዝርያዎችን እና የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በመጠቀም፣ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን እና አሠራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ለሰሊጥ ምርታማነት ማደግ ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።

አቶ አንዳርጌ እንዳሉት 107 ሺህ ሄክታር መሬት በአምራች አርሶ አደሮች እና 70 ሺህ ሄክታር መሬት በአልሚ ባለሃብቶች የሰሊጥ ዘር የተሸፈነ እንደኾነም ነው የገለጹት፡፡

በዞኑ በመኽር ወቅት በሰሊጥ የለማው መሬት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ16 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ብልጫ እንዳለውም አመልክተዋል።

ኀላፊው እንደገለጹት የሰሊጥ ልማቱ ከዕቅዱም ኾነ ካለፈው ዓመት ጭማሪ ያሳየው ምርታማነቱ እና ግብይቱ እያደገ በመምጣቱ አልሚዎችን የበለጠ ተጠቃሚ እያደረገ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ እንደኾነ አብራርተዋል።

በዞኑ ባለፈው የመኸር ወቅት 135 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በሰሊጥ ለማልማት ዕቅድ ተይዞ ከ160 ሺህ ሄክትር መሬት በላይ መልማቱን ከመምሪያው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ የአምስት ቀበሌ ኅብረተሰብን የሚያገናኝ ተንጠልጣይ ድልድይ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።
Next articleከ390 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በሰሜን ወሎ ዞን የተገነቡት የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ::