በሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ የአምስት ቀበሌ ኅብረተሰብን የሚያገናኝ ተንጠልጣይ ድልድይ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።

60

ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)አቶ አራጋው እንዳለው በጠለምት ወረዳ የአዲብረት ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። በቀበሌያቸው የሚገኘው ደበልጋይ ወንዝን ለመሻገር አስቸጋሪ እንደነበር ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት 20 የሚኾኑ ሰዎች እና በርካታ ቁጥር ያለው እንስሳት በወንዙ መወሰዳቸውን አስታውሰዋል። በዚህም ምክንያት ክረምት በመጣ ቁጥር በአካባቢው ተንቀሳቅሶ ለመሥራትም ኾነ ማኅበራዊ ኑሮን ለመከወን አስቸጋሪ እንደነበር ጠቅሰዋል።

ተማሪዎች ወንዙ ካልጎደለ ወደ ትምህርት ቤት ለመጓዝ ይቸገሩ እንደነበርም ተናግረዋል። ሕዝቡ ድልድይ እንዲሠራለት ሲጠይቅ የኖረ ቢኾንም ሳይሳካ ቆይቷል ያሉት አቶ አራጋው አሁን ግን ጊዜው ደርሶ ድልድዩ ስለተገነባልን ደስታችን ወደር የለውም ብለዋል።

የጠለምት ወረዳ መንገድ እና ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አበባው ውበት በአዲብረት ቀበሌ በደበልጋይ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ የአምስት ቀበሌዎች 23 ሺህ ሕዝብ የሚያገለግል መኾኑን ገልጸዋል።

ድልድዩ መጋቢት 2016 ዓ.ም ተጀምሮ በሦስት ወራት ተጠናቅቋል። ሐምሌ 12 ቀን 2016 ዓ.ም የተመረቀው ይሄው ድልድይ ከእንግዲህ ለሕዝቡ ጌጥ እንጂ ስጋትነቱ ተቀርፏል ነው ያሉት ኀላፊው።

ድልድዩ 76 ሜትር ርዝመት እንዳለው እና 5 ሚሊዮን ብር እንደወጣበት ከአማራ ክልል መንገድ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ታደሰ ይርዳው ቢሯቸው ለድልድዩ 80 በመቶ ወጪውን መሸፈኑን እና በባለሙያ ክትትል ማድረጉን ገልጸዋል። ቀሪውን 20 በመቶ ወጪ ሄልቬታስ የተባለ በጎ አድራጊ ድርጅት ሸፍኖታል ብለዋል። የጉልበት ሥራው ደግሞ በማኅበረሰቡ መሸፈኑ ታውቋል።

አቶ ታደሰ በ2016 በጀት ዓመት በክልሉ 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር እና በፌዴራል መንግሥት ደግሞ 96 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቦ የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ሲሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በፌዴራል መንግሥት ሊሠሩ ከታቀዱ 65 ፕሮጀክቶች ውስጥ 31ዱ ሥራ ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥም 107 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ተሠርቷል ብለዋል።

34ቱ ፕሮጀክቶች ግን በጸጥታ እና ሌሎች ችግሮች ምክንያት አለመጀመራቸውን ገልጸዋል። 12 ነጥብ 9 ሺህ ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ጥገናም በፌዴራል እና የክልሉ መንግሥት መከናወኑን ነው ያስገነዘቡት።

በክልሉ መንግሥት 24 ተንጠልጣይ ድልድይ፣ 14 የኮንክሪት ድልድይ፣ 63 መለስተኛ እና ዝቅተኛ ድልድዮች፣ 89 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ መሠራቱን አቶ ታደሰ ጠቅሰዋል።

ኅብረተሰቡም 801 ሚሊዮን ብር በማዋጣት 265 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ መሥራቱን ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጠንካራ ዲሞክራሲ መሠረት ላይ የቆመ ሀገር እንዲኖር እና በእኩልነት ለመዳኘት ጠንካራ የዳኝነት ሥርዓት መገንባት ያስፈልጋል” ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር)
Next articleከ150 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥ ምርት ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡