
ባሕር ዳር: ሐምሌ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም ገምግሟል፡፡
የምክር ቤቱ የሕግ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) የፍትሕ ዘርፉ አሁን ካለበት የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖረው ተጨማሪ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
ሙያዊ የኾኑ፣ ከመብት ጋር የተያያዙ፣ የዳኝነት ሥርዓቱን ለማሳለጥ የሚያግዙ ጎዳዮች ላይ ቋሚ ኮሚቴው ይሠራል ነው ያሉት፡፡
ጠንካራ ዲሞክራሲ መሠረት ላይ የቆመ ሀገር እንዲኖር፣ በእኩልነት ለመዳኘት፣ በፍትሕ ዘርፉ የሚታዩ ችግሮች ታርመው ዜጎች ዕምነት የሚጥሉባቸው ተቋማትን ለመገንባት ጠንካራ የዳኝነት ሥርዓት መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የዳኝነት ነጻነትን ማክበር እና ማጥበቅ አስፈላጊ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ ዳኞች ሕግን እና ማስረጃን መሠረት አድርገው የመወሰን ግላዊ ነጻነታቸው የተወሰነ ነው፣ ካጠፉ እና የሥነ ምግባር ጉድለት ካለባቸው ደግሞ ተጠያቂነት አለባቸው ነው ያሉት፡፡
ዳኞች ላይ የሚደርስ እንግልት መታረም ያለበት እና ድርጊቱን የሚፈጽሙ አካላት ተጠያቂ መኾን እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል፡፡ ዳኞች ላይ የሚደርስ እንግልት እና ወከባ የፍትሕ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል መኾኑን ነው ያነሱት፡፡
ነጻነትን ከተጠያቂነት ጋር አመዛዝኖ ማየት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል፡፡ የዳኝነት ነጻነት የተሰጠው ለሕዝቡ ጥቅም ሲባል መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ምክር ቤቱ በአጽንኦት እንደሚሠራባቸውም ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልሉ ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ውስጥ መልካም መልካም ተግባራትን መፈጸሙንም አመላክተዋል፡፡ የተሻለ ተቋማዊ አሠራር ለመፍጠር ያደረገው ሥራ የሚበረታታ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ነጻ ፍትሐዊ እና ተዳራሽ የኾነ የዳኝነት አገልግሎት ለኅብረተሰቡ መስጠት የሚያስችል ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባቱንም አንስተዋል፡፡ የዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች የሙያ ሥነ ምግባር ማሻሻያ ደንብ እየተሠራ መኾኑ በመልካም የሚነሳ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡
የፍርድ ቤትን ተደራሽነት ለማሻሻል የተሠሩ ሥራዎችም የሚበረታቱ መኾናቸውን ነው ያመላከቱት፡፡ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የርቀት ሙግት ሥርዓትን ለማጠናከር እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች በጥንካሬ የሚታዩ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡ በተዘዋዋሪ ችሎት እና በምድብ ችሎት የተፈጸሙ ተግባራትም የሚበረታቱ መኾናቸውን ነው የገለጹት፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ጨምሮ በወልቃይት ጠገዴ፣ በጠለምት፣ በወፍላ ኮረም እና ራያ አላማጣ እስከ 10 የሚደርሱ የወረዳ ፍርድ ቤቶች በአዲስ መልክ ተደራጅተው ወደ ሥራ መግባታቸው ትርጉማቸው ዘርፈ ብዙ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ለዘመናት የፍትሕ ጥያቄ ያለበትን ማኅበረሰብ ተደራሽ ማድረጉ የሚደነቅ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
በፍርድ ቤቶች ውሳኔ የሚያገኙ መዛግብት ከብዛት፣ ከጥራት፣ ከጊዜ እና ከውጤታማነት አኳያ ያሉ ሥራዎች አበረታች ናቸው ተብሏል፡፡ በፍርድ ቤቶች ውሳኔ የሚሰጣቸው መዛግብት እየጨመሩ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
94 ነጥብ 58 በመቶ የሚኾኑ መዝገቦች ከስድስት ወር በታች ውሳኔ ማግኘታቸውን ነው ያመላከቱት፡፡ የመዛግብት የማጣራት አቅም አፈጻጸም ጥሩ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
በዳኞች መካከል የሚታዩ የሥነ ምግባር ጉለቶችን ሕግ እና ሥርዓት በሚፈቅደው መሠረት ለማረም የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት፡፡ የዳኝነት ሥርዓቱ ክልሉ በገጠመው የሰላም እጦት ምክንያት መጎዳቱን የተናገሩት ሠብሣቢው እስካሁን ድረስ ወደ ሥራ ያልገቡ ፍርድ ቤቶች መኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ምስጉን እና በሕዝብ ዘንድ የሚታመኑ ዳኞች ያሉበት ሥርዓት እየገነቡ ለመሄድ ሕግን መሠረት እያደረጉ ሰፊ ሥራዎች መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
የርቀት የሙግት ሥርዓት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ከሳሽ እና ምስክር ያልተገኘባቸውን መዛግብት የሚዘጉበትን ሁኔታ በጥንቃቄ ማየት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ቋሚ ኮሚቴውም በትኩረት እንደሚከታተለውም አስታውቀዋል፡፡
የዳኝነት ነጻነትን የሚጎዱ ያልተገቡ ተግባራት በፍጥነት ሊታረሙ ይገባል ያሉት ሠብሣቢው ምክር ቤቱም በአጽንኦት ይከታተለዋል ነው ያሉት፡፡ ዳኞችን ማዋከብ ችሎት ከመድፈር ባለፈ ወንጀል መኾኑን ነው ያመላከቱት፡፡
የዳኞችን አቅም ማሳደግ በቀጣይ በትኩረት ሊሠራባቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሠራቸውን መልካም አፈጻጸም አጠናክሮ እንዲቀጥል እና ዝቅተኛ አፈጻጸም የታየባቸውን ደግሞ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!